DW Amharic
February 4, 2025 at 02:25 PM
የሉሲ ቅሪተ-አጽም በአውሮጳ ቤተ-መዘክር ለዕይታ ሊቀርብ ነው
በሰው ልጆች አፈጣጠር ሣይንሳዊ ምልከታ 3.18 ሚሊዮን ዓመት እድሜ እንዳለው የሚገመተው የሉሲ ወይንም ድንቅነሽ ቅሪተ-አጽም አውሮጳ ውስጥ ለዕይታ ሊቀርብ ነው ። በሰሜን ምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል አፋር ውስጥ ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት የተገኘው ይህ ቅሪተ-አካል ከዚህ ቀደም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለዕይታ ተወስዶ ነበር ። አሁን በአውሮጳ፤ ቼክ ዋና ከተማ ፕራኅ ብሔራዊ ቤተ-መዘክር ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕይታ ይቀርባል ተብሏል ።
የድንቅነሽ ቅሪተ-አጽም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዘክር በውሰት አውሮፓ ለዕይታ እንደሚቀርብ የቼክ ጠቅላይ ሚንስትር ፔትር ፊያላ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዐሳውቀዋል ። ከሉሲ በ100,000 ዓመት እንደምትበልጥ በሳይንሱ ዓለም የሚገመትላት «ሰላም» የተባለችው የአውስትራሎፒቲከስ ቅሪተ-አጽምም አብሮ ለዕይታ ይቀርባል ተብሏል ። የሰላም ቅሪተ-አጽም የድንቅነሽ በተገኘበት ሥፍራ የዛሬ 25 ዓመት ነው በቁፋሮ የወጣው ። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚንስትር ሠላማዊት ካሣ፦ «ይህ ታሪካዊ አውደ-ርዕይ …ለጎብኚዎች እና ተመራማሪዎች በሕይወት አንዴ የሚገኝ አጋጣሚ ያመቻቻል» ማለታቸውን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ።
በሳይንሱ ዓለም በሁለት እግሯ ቀጥ ብላ የምትራመድ ጥንታዊቷ ተብላ ትገመት የነበረችው ሉሲ ከዛፍ ላይ ወድቃ ስትሞት ዕድሜዋ 11 አለያም 13 እንደነበር ይነገራል ። ከ31 ዓመታት በፊት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘችው «አርዲ» የተባለች ሌላ ቅሪተ-አጽም በ4,5 ሚሊዮን ዕድሜዋ ከሉሲ መብለጧ ይዘገባል ። ከ24 ዓመታት በኋላ ግን ቻድ ውስጥ የተገኘው «ቶማይ» የተሰኘው የሰው ልጅ የራስ ቅል ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ዓመት ቅድሜ በማስቆጠር ጥንታዊው ቅሪተ-አጽም እንደሆነ ይነገርለታል ።
🙏
1