
DW Amharic
185.2K subscribers
Verified ChannelAbout DW Amharic
ውድ የዶይቸ ቬለ የዋትስዓፕ ተከታታዮች የተለያዩ መገናኛ አውታሮችን በመጠቀም አድማሳችንን በማስፋት ዝግጅቶቻችንን አሁን በዋትስዓፕም ማቅረብ ጀምረናል።
Similar Channels
Swipe to see more
Posts

የጎርፍ አደጋ በህንድ በህንድ የጉጅራት ግዛት በአለፈው ሰኞ በጣለው ከባድ ዝናብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18 መድረሱን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ። በአካባቢው ሌላ ከፍተኛ ዝናብ ስለሚጠበቅ መንግስት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን ወደ አካባቢው አንቀሳቅሷል። በዕለቱ የጣለው ዝናብ በ24 ሰዓታት ውስጥ 34 ኢንች ተመዝግ።ል። ይህም በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል። ከአደጋው በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ሕይወት መታደጉን መንግስት መግለጹን የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር ተወያዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ። ፓርቲዎቹ እያንዳንዳቸው አራት ተወካዮችን በውይይቱ እንዲያሳትፉ ዕድል ተሰጥቷቸዋል። በሌላ በኩል ግብዣውን ያልተቀበሉ፣ በውይይቱም ያልተሳተፉ ፓርቲዎች መኖራቸው ታውቃል። በውይይቱ ከተሳተፉ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ኢሕአፓ "ጥያቄ የመጠየቅ ዕድል አላገኘሁም፣ በሌሎች ፓርቲዎች የቀረቡ ጥያቄዎችም መሠረታዊ አይደሉም" በሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከመስጠታቸው በፊት ተወካዮቹ መድረክ ረግጠው መውጣታቸውን አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ "ከየመጡበት አካባቢ የሚነሱ የተለያዩ ሀሳቦችን በማዳመጥ ግብዓት ለመውሰድ የታለመ" ያሉትን ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል ሲል ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።


ሰላማዊ ሰልፍ በመቐለ መንግስት ድህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ወደቀዬአቸው የማይመልሳቸው ከሆነ የራሳቸው እርምጃ እንደሚወስዱ በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ገለፁ። በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች በመንግስት ላይ ተቃውሟቸው የሚገልፁበት ትእይንት ዛሬ በመቐለ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን በመጪው ዓርብ የዚሁ አካል የተባለ ሰልፍ በጄኔቫ እንደሚደረግ አስተባባሪዎች አስታውቋል። ተፈናቀዮቹ ዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀንና ለሊት የሚቆይ ተቃውሞ በመቐለ ሮማናት አደባባይ ማድረግ የጀመሩት እነዚህ የጦርነቱ ተፈናቃዮች፥ ለአምስተኛ ክረምት በመጠለያ መቆየት እንደማይሹ፥ የኢትዮጵያ መንግስት እና የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ለጉዳያቸው የመጨረሻ ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ የራሳቸው እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀዋል ሲል ሚልዮን ሃይለስላሴ ከመቐለ ዘግቧል።


ኢራን ከእስራኤል የስለላ ድርጅት «ሞሳድ» ጋር አብረዋል ብላ የጠረጠረቻቸው 5 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋልዋን አስታውቃለች። ተጠርጣሪዎቹ የኢራንን ወቅታዊ ሁኔታ የሚመለከቱ መረጃዎችን በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲያሰራጩ ነበር ስትል ወንጅላለች። ኢራን እንዳለችው «እነዚህ ቅጥረኞች በኢራን ሕዝብ መካከል ፍርሃትን ለመንዛትና የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የተቀደሰ ሥርዓትን ለማጠልሸት ሲሰሩ ነበረ።» ተጠርጣሪዎቹ የታሰሩት መምዕራብ የኢራን ግዛት መሆኑን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።


የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ሐገራቸው በኢራን ላይ የምትፈፅመው ጥቃት የኒኩለር መርሃ ግብሯን ለማስቆም ብቻ ሳይሆን የመንግስት አመራሩንም ለማፈራረስም ያለመ ነው አሉ። የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር በኤክስ ገጻቸውን የጻፉትን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው «አምባገነን መንግስታት የሚወድቁት በዚሁ መንገድ ነው» ብለዋል። እስራኤል በአለፈው ሰኞ በቀጥታ ሥርጭት ላይ የነበረን አንድ መንግስታዊ የቴሌቪዥን ጣብያን በቦምብ አጥቅታለች። በጥቃቱ በቁጥር ያልተገለጹ በርካታ ሰዎች መሞት መቁሰላቸውን ዜናው አክሏል። እስራኤል በቴህራን ወታደራዊ ተቋማት አካባቢ የሚኖሩ ኢራናውያን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በሰቸችው ማሳሰቢያ መሰረት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እየወጡ እንደሆነ ዘገባዎች ያመላክታሉ። የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካመኒ ከተወሰኑ ሰዓታታት በኋላ በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።


ውድ አድማጮች የዶይቸ ቬለ የዩቲዩብ ገጻችን ይከተሉ! ለባለንጀራዎም ያጋሩ! የትክክለኛው የዶይቸ ቬለ ዩቲዩብ ገጽ አባል በመሆን ዝግጅታችንን ተከታተሉ ። በትክክለኛው በዚህ የዩቲዩብ አድራሻችን፦ https://www.youtube.com/channel/UC3-RNH75BEZslJLEoIAxa2A አባል ይሁኑ ። ለወዳጆቻችሁም ያጋሩ ።

የሥርጭት ማስታወቂያ ሰላም ጤና ይስጥልኝ ውድ አድማጮች እንደምን አላችሁ? በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ልክ 1 ሰዓት ላይ የሚጀምረው የዛሬው ሥርጭታችን እንደተለመደው የዓለማችን ዓበይት ዜናዎችን በማቅረብ ይጀምራል። ዜናውን ተከትሎ በሚቀርበው የዜና መፅሔታችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ከሐገሪቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያካሄዱት ውይይት፤ መንግስት በየዕለቱ ከባንክ የሚወጣውን የገንዘብ መጠን መገደቡን፤ በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሰላማዊ ሰልፍ፤ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚኖሩ ተፈናቃዮች ስሞታ የሚሉ ርዕሶች ተካተዋል። ሳምንታዊ ዝግጅቶች ከኢኮኖሚው ዓለምና ሳይንስና ቴክኖሎጂም ሰዓታቸውን ጠብቀው ይቀርባሉ። አብራችሁን እንድትሆኑ ከወዲሁ በአክብሮት እንጋብዛለን።


እስራኤል በቴህራን የሚገኘውን የሐገር ውስጥ ደህንነት መስሪያቤት ማውደሟን አስታወቀች። የእስራኤል ሰራዊት ዛሬ ባሰራጨው መረጃ «የሐገር ውስጥ የደህንነት መስሪያቤቱን ያወደምኩት በጦር አውሮፕላኖች ድብደባ ነው» ብሏል። ሰራዊቱ ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ በኢራን ላይ የሚካሄዱ ጥቃቶች አላማ የኒኩለር ማብለያ ተቋማትን ማውደም ብቻ ሳይሆን «አምባገነን» ያለውን የኢራንን መንግስታዊ መዋቅሮችንም እንደሚያካትት ገልጾ ነበር ሲል አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።


የተፈናቃዮች ስሞታ ባለፉት አምስት ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን እና ሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ 15 የመጠለያ ጣቢያዎች እና ማህበረሰቡ ጋር በመንግስት እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚደረግላቸው ድጋፍ ኑሯቸውን የሚመሩ ከ65000 (ስልሳ አምስት ሺ) በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡ በተለይም በባለፉት 2 አመታት የድጋፍ ሁኔታው መቃዘቀዝ የታየበት በመሆኑ እና በመንግስት የሚሰጠን ትኩረት አናሳ መሆን ኑሯችንን በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለመምራት ስላላስቻለን ቀድመን በተወለድንበት ሀብት ንብረት ባፈራንበት አካባቢ ተመልሰን እንድንሰራ መንግስት ሊያመቻችልን ይገባል ሲሉ በተሁለደሬ ወረዳ ጃሪ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያሉ ተፈናቃዮች ለዶይቼቨለ ተናግረዋል፡፡ በ11መጠለያ ጣቢያዎች እና ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖሩ ከ34,000 በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የያዘው የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ከዚህ ቀደም ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሙከራ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም ማለታቸውን ወኪላችን ኢሳያስ ገላው ከደሴ ዘግቧል፡፡


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት« የመርማሪዎችን የወንጀል ተጠያቂነት ያጠበበ» የሚል ጥያቄ የተነሳበት ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በ3 ተቃውሞና በ1 ድምፀ ተዐቅቦ በአብላጫ ድንፅ አፅድቆታል። በዚህ ዐዋጅ መሠረት መሰል ወንጀሎችን ለመመርመር የተመደበ ሰው በሥራ ላይ እያለ "ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም" በሚል መደንገጉ ጥያቄ አስነስቷል። ይህ ድንጋጌ በምርመራ ሽፋን የመንግሥት ተቃዋሚዎችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ ጋዜጠኞችን እና ነጋዴዎችን ለማጥቃት የተረቀቀ እና የዜጎችን መብት የሚጎዳ ነው የሚል ተቃውሞ ገጥሞታል። አዋጁን ያዘጋጁት አካላት ግን የሕጉ መንፈስ ይህ አለመሆኑን ጠቅሰው አላማው ሽብርተኝነትን መከላከል ነው ብለዋል። እናንተስ ምን ትላላችሁ? ተወያዩበት።
