Meseret Media
Meseret Media
February 17, 2025 at 03:07 PM
ባሳለፍነው ሳምንት ሸራተን ሆቴል አቅራቢያ ከፍተኛ የፍንዳታ አቅም ያለው ፈንጂ ተገኝቶ እንደነበር ታወቀ (መሠረት ሚድያ)- ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ ሸራተን ሆቴል አቅራቢያ ከፍተኛ የፍንዳታ አቅም ያለው ፈንጂ በአሰሳ ወቅት ተገኝቶ እንደነበር ታውቋል። እሮብ እለት፣ ማለትም የካቲት 6/2017 ዓ/ም ምሽት አምስት ሰአት ላይ ከቤተመንግስት አቅጣጫ ወደ ሸራተን መውረጃ ጠመዝማዛው መንገድ አቅራቢያ TNT የተባለ ፈንጂ መገኘቱን የፀጥታ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ አረጋግጠዋል። የፈንጂው መገኘት አሁን ላይ ከተጠናቀቀው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጋር የተገናኘ ይሁን አይሁን እስካሁን ይፋ አልተደረገም። ሚድያችን በዚህ ዙርያ ተጨማሪ መረጃ ከፌደራል ፖሊስ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ የጠየቀ ቢሆንም "መረጃው የለንም" የሚል ምላሽ አግኝቷል። ይሁንና የፌደራል ፖሊስ ባሳለፍነው ሀሙስ፣ ወይም ፈንጂው ከተገኘበት ከአንድ ቀን በኋላ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ባቀረበው ክስ 13 ሰዎችን የአፍሪካ ህብረት የሚታደሙ ሰዎችን ለማጥቃት በማሴር ክስ መስርቷል። ክሱ በግልፅ ድርጊቱ ይህ ሸራተን አካባቢ ጋር ከተገኘው ፈንጂ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ባይጠቅስም "የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አባል ሀገራት እና ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ስብሰባው ላይ ለመታደም በሚመጡ አመራሮች እና ጋዜጠኞች ላይ የሽብር ጥቃት እንዲፈፅሙ" ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ይገልፃል። በዚህ ዙርያ የመንግስት አካላት መግለጫ ሊሰጡ እየተዘጋጁ እንደሆኑ የደረሰን ተጨማሪ መረጃ ይጠቁማል። መረጃን ከመሠረት!
Image from Meseret Media: ባሳለፍነው ሳምንት ሸራተን ሆቴል አቅራቢያ ከፍተኛ የፍንዳታ አቅም ያለው ፈንጂ ተገኝቶ እንደነበር ታወቀ   (መ...
👍 1

Comments