Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
February 26, 2025 at 09:37 AM
*በኦሮሚያ ክልል መቱ ከተማ ነዳጅ በሊትር እስከ 900 ብር እየተሸጠ መሆኑ በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ አስነሳ* 👉 የክልሉ ንግድ ቢሮ በዚህ መልኩ የተጋነነ የጥቁር ገበያ የለም ብሏል የካቲት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል መቱ ከተማ ነዳጅ በሊትር እስከ 900 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተከትሎ፤ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው እንደሚገኝ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡ የነዳጅ አቅርቦት በማደያዎች ባለመኖሩ በጥቁር ገበያ እየተሸጠ እንደሚገኝ ያነሱት ነዋሪዎቹ፤ በተለይ በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፉ ላይ ጫናው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ጭማሪ በተያዘው ወር ማለትም የካቲት 2017 ዓ.ም ከገባ ጀምሮ እየተባባሰ የመጣ መሆኑን የገለጹም ሲሆን፤ "ችግሩን በመረዳት የሚመለከተው አካል የነዳጅ አቅርቦት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡  በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ፣ በወላይታ፣ በጎፋ ዞኖች 1 ሊትር ነዳጅ በሕገ-ወጥ መንገድ ከ500 ብር በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ አሐዱም በኦሮሚያ ክልል ያለው ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን በተመለከተ የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ የንግድና ኢንስፔክሽን ዋና ዳይክተር አቶ ጌታቸው ቆጲሳን አነጋግሯል፡፡ በምላሻቸውም በክልሉ ብሎም በመቱ ከተማ ያለው የነዳጅ እጥረት እንደ ሀገር የተከሰተ መሆኑን አንስተው፤ "በሕገ-ወጥ መንገድ እስከ 900 ብር የሚሸጥበት ሁኔታ ግን የለም" ብለዋል፡፡ አክለውም ይህ ችግር እንዳይፈጠር እንደ ክልል ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ግብረ ሃይል በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አንስተው፤ በዚህ መልኩ የተጋነነ የጥቁር ገበያ እንደሌለ እና ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይም እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ አሐዱም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለው የሕገ-ወጥ ነዳጅ ግብይትን በተመለከተ የክልሉ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሳዲሁንን ጠይቋል፡፡ ምክትል ኃላፊው በምላሻቸው ከዚህ በፊት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት ተበራክቶ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በአንጻሩ የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ አለ ብለዋል፡፡ አክለውም ይህንን የጥቁር ገበያ ቁጥጥር ለማድረግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለማስቀረት ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ትብብር በማድረግ ያሉትን ግብአቶች በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ በአለምነው ሹሙ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *በኦሮሚያ ክልል መቱ ከተማ ነዳጅ በሊትር እስከ 900 ብር እየተሸጠ መሆኑ በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ አስነሳ*  ...

Comments