Ahadu Radio And Television
February 26, 2025 at 11:57 AM
*በኦሮሚያ ክልል ከእንስሳት አደን በዓመት 13 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ ተገለጸ*
የካቲት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ ከዱር እንስሳት ዘርፍ በዓመት አማካይ ወደ 18 ሚሊዮን ብር የሚገኝ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ከፍተኛውን መጠን የያዘውና ወደ 13 ሚሊዮን ብር ገቢ የሚገኘው ከአደን መሆኑን የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት አስታውቋል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አራርሳ ረጋሳ አደንን በተመለከተ 'እንስሳትን ይጎዳል' በሚል የሚከለክሉና በሌላ በኩል ሥራውን የሚደግፉ አካላት መኖራቸውን በመጥቀስ፤ እንደ ኦሮሚያ ክልል በተጨባጭ በተለይም 'ስፖርታዊ አደን' የሚባለው በጥንቃቄ በመሰራቱ ደኖች ከመመናመን ይልቅ እየለሙ እንዲመጡ መደረጉን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ጥንቃቄ ስለማይደረግ ደኖች ቀስ በቀስ ወደ እርሻነት እየተቀየሩ የዱር እንስሳቱም ሊጠፉ የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበረ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ግን ጎብኚዎች እንዲገቡ በማድረግ ከገቢ ጋር እንዲያያዝ በመደረጉ የተሻለ ገንዘብን ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከገቢ በዘለለም ቦታዎቹን በመንከባከብ ጥብቅ ደኖች እንዲሆኑ ማደረግ እየተቻለ መሆኑን አክለዋል።
በተጨማሪም አደኑ ሲሰራ በጥንቃቄ እንስሳቶች ተለይተው፣ ኅብረተሰቡም እንዲያውቅ ተደርጎና ከክልሉና ከፌዴራል የተውጣጣ የባለሙያ ቡድን ተመድቦ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የእንስሳቱ ቆጠራ ተካሂዶ፣ በበቂ ሁኔታ መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ቦታ ተወስኖለት እና ቁጥር ተመድቦለት አደኑ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
"ተለይተው ለአደን ከሚቀርቡት እንስሳት መካከል ሴቶችና በእድሜ ያልገፉት ተመርጠው የተዋልዶ መጠን ላይ ብዙ ጥቅም የሌላቸው ያረጁ እንስሳት ብቻ ይታደናሉ" ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በመሆኑም የእንስሳቱ አደን በጥንቃቄ ስለሚሰራና 'ጥቅም እንጂ ጉዳት' የሌለው መሆኑን በመግለጽ፤ በአደን ከሚገኘው ገንዘብ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ለማኅበረሰቡ ተመልሶ ገቢ የሚደረግ መሆኑን አመላክተዋል።
"በዱር እንስሳት ሀብት የታደልን ብንሆንም ግን መንከባከብና ማስተዋወቅ ባለመቻላችን፤ ተጠቃሚ ስላልሆንን በርካታ ሥራዎች መስራት ይጠበቅብናል" ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የእንስሳት አደንን በሚመለከት አሁን ላይ የአደን ቦታዎች እየተስፋፉ ቢሄዱ ከዚህም በላይ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን በበጀት ዓመቱ ሥድስት ወራት ከዱር እንስሳት ዘርፍ ከ62 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ማገኘቱን በመግለጽ፤ ከተገኘው ገቢ 49 ነጥብ 8 ሚሊየን ያህሉ ከዱር እንስሳት ፍጆታዊ አጠቃቀም ወይንም ሕጋዊ አደን የተገኘ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ