Ahadu Radio And Television
                                
                            
                            
                    
                                
                                
                                February 26, 2025 at 03:36 PM
                               
                            
                        
                            *ኢትዮ- ቴሌኮም የእንስሳት አያያዝን የሚያዘምን እና የሚገኙበት ቦታ በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችል አዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ* 
👉በተጨማሪም ስድስት ሌሎች የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖች ይፋ ተደርገዋል
የካቲት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የቴሌኮም እና ዲጂታል ሶሉሽኖች አቅራቢ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በላቀ አይ.ኦቲ (IoT) የተደገፈ እና የኡትዮጵያን የእንሰሳት አስተዳደር ለማዘመን የሚያስችል ዲጂታል የእንሰሳት መከታተያ ሶሉሽን በዛሬው ዕለት በተጀመረው የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖቹ አውደ ርዕይ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የእንስሳትን ደህንነት ለማሻሻል በተለይም የእንስሳት ባለቤቶች የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የፋይናንስ ተደራሽነት ክፍተት ለማጥበብ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡
ሶሉሽኑ አርሶ አደሮች እና እንሰሳት አርቢዎች በቀላሉ እንስሳቶቻቸውን መከታተል፣ ያሉበትን ቦታ መለየት እና የጤና ሁኔታቸውን መገምገም እንዲችሉ እንዲሁም፤ ውጤታማነትን፣ ደህንነትን እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን እንዲያረጋግጡ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በእንስሳት ብዛት 70 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚገመቱ የቀንድ ከብቶች፣ 95 ነጥብ 4 ሚሊዮን በግና ፍየሎች እንዲሁም 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ግመሎች መገኛ በመሆን በአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም፤ ዘርፉ ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ ፈተናዎችና ችግሮች ሲገጥሙት መቆየታቸው ይታወቃል። 
ይህ አዲሱ የኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል የእንስሳት መከታተያ 'ዲጂታል ላይቭስቶክ ትራኪንግ ሶሉሽን' (digital cattle tracking solution) በቀጥታ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳትን አያያዝ ዘዴን በማቅረብ በዘርፉ ሲያጋጠሙ የነበሩ ተግዳሮቶች የሚቀርፍ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በዚህም መሰረት ዲጂታል የእንስሳት መከታተያው በእንስሳት በጆሮ ላይ በሚገጠሙ መለያዎች አማካኝነት ወሳኝ መረጃዎችን የሚመዘግቡ አነስተኛ የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች ልዩ የእንስሳት ዝርዝር መለያዎችን፣ ቀለማቸውን፣ ጾታቸውን፣ የተወለዱበትን ቀንና ዕድሜያቸውን እንደሚመዘግቡ ተገልጿል። 
በተጨማሪም የእያንዳንዱን እንስሳት መገኛ ቦታን በቀላሉ ለመከታተል ወይም ለመለየት ያስችላሉ ተብሏል።
ስለእንስሳቱ ሁለንተናዊ መረጃን መስጠት የሚያስችል ራቅ ባሉ አካባቢዎች ቢጓዙ ወይም ቢጠፉ የት እንደሚገኙ ለማወቅ በቀላሉ ተከታትሎ መረጃ የማቅረብ አቅም ያለው መሆኑም ተገልጿል።
ይህ መረጃ ለአጠቃቀም ምቹ በሆነ ሥርዓት ከሲስተም ጋር ተቀናጅቶ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በድረ-ገጽ በታገዘ የመድን ስርዓት እና ለመስክ ሠራተኞች ወይም የድርጅት ወኪሎች በተዘጋጀ የሞባይል መተግበሪያ ተደራሽ እንደሚሆንም ተቋሙ ለአሐዱ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በዚሕም አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት የእንስሳት ሀብታቸው ያሉበት ቦታና ደረጃን በመከታተል የእንስሳት አያያዝን ለማሻሻል እና የሚደርስባቸውን ኪሳራ ለመቀነስ ይችላሉ ተብሏል፡፡ 
በሶልሽኑ በተረጋገጠ መረጃ በመታገዝ ባንኮች እና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንስሳቱን እንደ መያዣ በመቀበል የብድር እና የመድን ዋስትና አገልግሎትን ለመስጠት አመኔታ እንዲኖራቸው እንደሚያስችላቸውም ተነግሯል።      
በተጨማሪም ሶሉሽኑ 'የኢንሹራንስ ይገባኛል' ጥያቄ ሂደቱን ስለሚያቃልል እና ስለሚያፋጥን በካሳ አከፋፈል ረገድ የሚከሰት አለመግባባትን እና ማጭበርበርን እንደሚቀንስ ተመላክቷል።·       
እንዲሁም የተሰበሰበው መረጃ ለፖሊሲ ቀረጻ እና ሀብት ድልድል ጠቃሚ ዕይታዎችን በመስጠት በእንስሳት ዘርፍ ለዘላቂ ልማት ዕገዛ እንደሚያደርግ ተቋሙ ገልጿል።        
ይህም ሶሉሽን ከኢትዮ-ቴሌኮም የቴሌብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ጋር ሙሉ ትስስር ስላለው ቀላል፣ ምቹና ፈጣን ግብይት እንዲኖር እንደሚያስችልም ተነግሯል።  ·      
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም:-
👉 አንድን ቁልፍ ብቻ በመንካት/በመጫን ከግለሰቦች ወይም ቡድኖች ጋር ቅጽበታዊ የድምጽ እና የቪዲዮ ግንኙነት ማድረግ የሚያስችል (ቴሌ ፑሽ-ቱ-ቶክ/ቪዲዮ ሶሉሽን)፣ 
👉 በክላውድ ላይ የተመሰረተ ኮር ባንኪንግ ሶሉሽን የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን እና የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራትን በዘመናዊ የዲጂታል ፋይናንሺያል መሳሪያዎች ለማስታጠቅ የሚያስችል (ኮር ባንኪንግ ሶሉሽን)፣  
👉 ሁሉን አቀፍ፣ በክላውድ የተደገፈ፣ የትምህርት ቤት ስራዎችን ለማቀላጠፍ፣ ኮሙኒኬሽኖችን ለማጎልበት እና የትምህርት ማኔጅመንት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል (የትምህርት አመራር ስርዓት ሶሉሽን)፣
👉 የቢዝነስ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ፣ የቡድን ሥራን ለማጎልበትና ለማዘመን እንዲሁም የሥራ ጥራትን እና ቅልጥፍናን ለማምጣት የሚያስችል ሁለገብ የሆነ የዲጂታል ፕላትፎርም (የአንድ ቢሮ ትብብር እና ምርታማነት ሶሉሽን)፣ 
👉 ኢትዮ ቴሌኮም የቢዝነሶችን የደንበኞች ግንኙነት የሚቀይር፣ በክላውድ ላይ የተመሰረተ እና ዘመናዊ ቴሌ የጥሪ ማዕከልን ፕላትፎርም (ቴሌ ኮንታክት ሴንተር ሶሉሽን)
👉 እንዲሁም የድርጅት ደንበኞች አሰራራቸውን እንዲያቀላጥፉ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደታቸውን እንዲያሻሽሉ እና ዘላቂ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችልና በክላውድ ላይ የተመሰረተ (የኢ.አር.ፒ ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ ሶሉሽን)ን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል፡፡
እነዚህ በክላውድ የታገዙ የዲጂታል ሶሉሽኖች ድርጅቶች መሰረተ ልማት መገንባትም ሆነ የመረጃ ማዕከል መገንባት ሳያስፈልጋቸው በኢንተርኔት አማካይነት ሶሉሽኖቹን እንዲጠቀሙና የኦፕሬሽን ሥራቸውን በማስተዳደር ላይ ብቻ በማተኮር የቢዝነስ ተወዳዳሪነታቸው እና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም እስካሁን ከ456 በላይ የድርጅት ደንበኞችንና አጋሮችን በቴሌ ክላውድና በዳታ ማዕከል አገልግሎቶቻችን ተጠቃሚ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፤ ለባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የተቀናጀ በሰውሰራሽ አስተውሎት (AI) የተደገፈ የማርኬት ፕሌስ ሶሉሽን ማቅረቡንም አስታውቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* 
ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ 
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP 
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ