Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
February 26, 2025 at 03:37 PM
*በሱዳን ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ ከፍተኛ መኮንኖችን ጨምሮ 46 ሰዎች ሞቱ* የካቲት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሱዳን ኦምዱርማን ከተማ በሚገኝ የመኖሪያ ሥፍራ ላይ ወታደራዊ አውሮፕላን በተከስክሶ፤ ወታደራዊ መኮንኖች፣ እንዲሁም ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ እስካሁን 46 ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡ የአንቶኖቭ አውሮፕላን በኦምዱርማን ሕዝብ በሚበዛበት ካራሪ አውራጃ ላይ ተከስክሶ በርካታ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ ከሟቾች በተጨማሪ በአደጋው ቢያንስ 10 ሰዎች ቆስለዋል ሲል በመንግሥት የሚተዳደረው የካርቱም የመገናኛ ብዙሃን ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የሀገሪቱ ባለስልጣናት አውሮፕላኑ የተከሰከሰው የዋና ከተማዋ ካርቱም እህት ከተማ ከሆነችው ኦምዱርማን በስተሰሜን ከሚገኘው ዋዲ ሲይዲና የአየር ጣቢያ ሲነሳ መሆኑን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። በአደጋው የታጠቁ ሃይሎች እና ሲቪሎች መሞታቸውን የገለጹም ሲሆን፤ ነገር ግን የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ ይፋ አላደረጉም። የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በኦምዱርማን ወደሚገኘው 'ናው' ሆስፒታል መወሰዳቸውን አስታውቋል። ከሟቾቹ መካከል የመላ ካርቱም የቀድሞ ጦር አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ባህር አህመድ እና ሌተናል ኮሎኔል አዋድ አዩብ ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና የአውሮፕላኑ ሠራተኞች እንደሚገኙበት፤ አንድ ወታደራዊ ባለስልጣን መናገራቸውን ኤ.ፒ ዘግቧል። በጉዳዩ ላይ ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ባለስልጣኑ እንዳሉት ከሟቾቹ መካከል ሴቶች እና ሕጻናት የሚገኙበት ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል አምስት ወንድሞች እና እህቶች ሕይወታቸው አልፏል። በካራሪ ወረዳ በአል-ታውራ ሰፈር ላይ የተከሰከሰው አውሮፕላኑ፤ ወደ ቀይ ባህሯ ከተማ ፖርት ሱዳን በመጓዝ ላይ እንዳለ አደጋው እንዳጋጠመውም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የአቪዬሽን ደህንነት ሪከርድ ደካማ በሆነባት ሱዳን ውስጥ የአውሮፕላን አደጋ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ይገኛል። እ.ኤ.አ. በ 2020 በዳርፉር ምዕራባዊ ክልል የሩስያ አንቶኖቭ አን-12 ወታደራዊ አይሮፕላን ተከስክሶ ቢያንስ 16 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ 2003 የሱዳን አየር መንገድ አውሮፕላን ድንገተኛ ሁኔታ ለማረፍ ሲሞክር ኮረብታ ላይ ወድቆ 8 የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 116 ሰዎች ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፤ ከአደጋው የተረፈው አንድ ልጅ ብቻ መሆኑ ተገልጿል። በእዮብ ውብነህ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *በሱዳን ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ ከፍተኛ መኮንኖችን ጨምሮ 46 ሰዎች ሞቱ*   የካቲት 19/2017 (አሐ...

Comments