Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
February 26, 2025 at 03:38 PM
*በባህላዊ መንገድ የሚመረቱ የወተት አቅርቦቶች ላይ የጥራት ችግሮች መኖሩ ተገለጸ* 👉ከውጭ የሚመጡ የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሰራ ነው ተብሏል የካቲት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በባህላዊ መንገድ የሚመረትና በቁጥር በውል የማይታወቅ የወተት ምርት ለማኅበረሰቡ ቀርቦ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፤ በዚህም የወተት አቅርቦቶች ላይ የጥራት ችግሮች መኖራቸውን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ለአሐዱ አስታውቋል፡፡ በኢንስቲትዩቱ የወተት ማቀንባበርና ጥራት ዘርፍ ረዳት ተመራማሪ አቶ ቅጣው ደግፈው፤ በባህላዊ መንገድ በአርብቶ አደሩ ወይንም በቤት ውስጥ ተመርተዉ ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡ እና የሚሸጡ የወተት ምርቶች ከአስተላለብ ጀምሮ በጽዳት አያያዝ እና ጥንቃቄዎች ላይ ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው ተገልጸዋል፡፡ ለዚህም በዋናነት ከሚስተዋሉ ችግሮች አንጻር የመኖ በበቂ ሁኔታ አለመቅረብ እና የእንሰሳት አያያዝ ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ ከዚህ አንጻር ኢንስቲቲዩቱ በአዲስ አበባ ዙሪያ፣ በአዳማ እና ቢሾፍቱ ላይ በጀመራቸዉ የቁጥጥር እና የስልጠና ሥራዎች ለውጥ ለማምጣት እየተሞከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን "አሁንም ዘርፉ ያላደገ በመሆኑ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ አልተቻለም" ብለዋል። "ከዚህ ጋር ተያይዞ በወተት ምርቶች በተለይም በባህላዊ መንገድ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ምርቶች ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሹ በመሆናቸው፤ ወተት አቅራቢዎች በቂ ስልጠናዎችን በመውሰድ ዘመናዊ አካሄዶችን ሊከተሉ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል። ይህ ማለት 'ሙሉ ለሙሉ ጥራት የጎደላቸዉ የወተት ምርቶች ገበያ ላይ አሉ' ማለት እንዳልሆነ እና ጥራት ያላቸው የወተት ምርቶች ስለመኖራቸው ያነሱት ረዳት ተመራማሪው፤ በኢንስቲትዩቱ በኩል የተጀመሩ ሥራዎችን በአዲስ አበባ እና በሌሎች ክልሎችም ተጠናክረው እንደሚሰሩ ጨምረው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ከውጭ ሀገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የወተት ተዋጽኦ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ለወጣቶች ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን አቶ ቅጣው ደግፈው ለአሐዱ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ምርቶቹን በሀገር ውስጥ ለመተካትም በቅድሚያ ከውጭ የሚመጡ ምርቶች ላይ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል። በዚህም ጥራቱን የጠበቀ በሆቴሎችና አየር መንገድ ጥቅም ላይ የሚውሉ የወተት ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል። ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ በመሆናቸው በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ደረጃ በዛው ልክ መሆን እንዳለበት አንስተው፤ "ይህን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ" ብለዋል። ለዚህም የወተት ጥራት ትልቁ ችግር መሆኑ ያነሱት ቅጣው የወተት ተዋጽዖቹ ጥራታቸው ዝቅ እንዲል እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። ለዚህም ከዓመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ወተት የሚሰበስብ ማንኛውም አካል ሰርተፊኬት ሊኖረው እንደሚገባ የወጣው መመሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ማውጣትና ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል። በፅዮን ይልማ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *በባህላዊ መንገድ የሚመረቱ የወተት አቅርቦቶች ላይ የጥራት ችግሮች መኖሩ ተገለጸ*   👉ከውጭ የሚመጡ የወተት...

Comments