Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
February 27, 2025 at 08:36 AM
*"ከዑምራ ተጓዦች ቪዛ ጋር በተያያዘ የወጡ ክልከላዎች ከሃጅ ጉዞ ጋር የሚገናኙ አይደለም" የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት* የካቲት 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት የቀሩት የዘንድሮ የሃጅ ጉዞ ምዝገባ ከጥር 15 ጀምሮ እስከ ነገ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚከናወን፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጹ ይታወቃል። በዚህም 'የሃጅ አዳዲስ ተጓዞችን ሳኡዲ አረቢያ አልቀበልም እያለች ነው' በሚል የወጣው መረጃ በተመለከተ፤ አሐዱ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን ጠይቋል። በምክር ቤቱ የሃጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ አብዱልፈታህ መሃመድ በሰጡት ምላሽ፤ ጉዳዩ የሃጅ ተጓዞችን ሳይሆን የዑምራ ተጓዦ ቪዛን የሚመለከት መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም "የሳኡዲ አረቢያ የሃጅ እና ኡምራ ሚኒስቴር ከውስጥ አሰራሩ ጋር በተያያዘና ካለው አገልግሎት የመስጠት አቅም ጋር በተያያዘ ነው ክልከላዎች ያስቀመጠው" ብለዋል። የሳኡዲ አረቢያ የሀጅ እና ኡምራ ሚኒስቴር የሀጅ ጉዞ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የሚመጡ ተጓዦች ቁጥር ከፍ እንዲል በማሰብ በየዓመቱ የተለያዩ ሥራዎችን የሚሰራ ሲሆን፤ ለዑምራ ተጓዦች የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ መስጠት መጀመሩም ይታወቃል። በዚህም የሃጅ ተጓዦችን አስመልክቶ ባወጣው አዲስ ጥብቅ መመሪያ፤ በሁሉም ሀገራት የሚገኙ የሃጅ ቢሮዎች ካሉባቸው ሀገራት ለሚመጡ የሃጅ ተጓዦች ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው እና ሚኒስቴሩ ያወጣቸውን ትዕዛዞች እና መመሪያዎች ማክበር እንዳለባቸው አሳስቧል። በተጨማሪም ተጓዦቹ ከመድረሳቸው በፊት የተጓዦቹን መረጃ ወደ ኤሌክትሪክ ስርዓት ማስገባት እና ተጓዦቹ የፖለቲካ ፍላጎት የሌላቸው እና ብጥብጥ የማይፈጥሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸውም በመመሪያው አሳስበዋል። በተጨማሪም መመሪያው ቢሮዎቹ ለሀጅ ተጓዦች የቀረቡ ትራንስፖርት አማራጮችን እና ሆቴሎችን ሳይፈቅድላቸው ከመጠቀም እንዲቆጠቡ እንዲሁም ከሃጅ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ የንግድ ወይም የድለላ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ክልከላ አድርጓል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ አብዱልፈታህ መሃመድ የሳውድ አረቢያ ሃጅ ሚኒስቴር ባስቀመጠውና መመሪያ መሰረት የተጓዦችን መረጃ የማደረጀት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ሚኒስቴሩ እና ጠቅላይ ምክር ቤቱ ይፋ ባደረገው ጊዜ ገደብ ውስጥ፤ በምዝገባ ጣቢያዎች በተሻለ አደረጃጀትና በተሟላ ግብዐት የምዝገባ አገልግሎት በመሰጠት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ ባደረገው ከፍተኛ ጥረትም እድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች ለሆኑ ሁጃጆች ይጠየቅ የነበረው የማስያዣ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር መደረጉን አንስተዋል፡፡ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ሃጅ ማድረግ ለሚሹ አካላት የሚከፈለውን ክፍያ ተመጣጣኝ ለማድረግም በጥናት ተመስርቶ 625 ሺሕ ብር እንዲሆን መወሰኑን አስታውሰዋል። በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ከፍተኛ 43 ሺሕ የሃጃጆች ኮታ የተሰጣት ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ማስታወቁ ይታወሳል። በፍርቱና ወልደአብ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *"ከዑምራ ተጓዦች ቪዛ ጋር በተያያዘ የወጡ ክልከላዎች ከሃጅ ጉዞ ጋር የሚገናኙ አይደለም" የእስልምና ጉዳዮች ...

Comments