
Ahadu Radio And Television
February 27, 2025 at 08:37 AM
*ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለይፋዊ ጉብኝት ሶማሊያ ገቡ*
የካቲት 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵይ እና ሶማሊያ መካከል የሻከረውን ግንኙነት ዳግም ለማደስ የሚደረገውን ጥረት ተከትሎ፤ ከፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ጋር ለመወያየት ዛሬ ሐሙስ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞቃዲሾ አዳን አብዱል ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፤ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የሶማሊያ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
ጉብኝቱ በሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤት ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ያልተረጋጋ ግንኙነት ለማርገብ እና ቀጣይ የግንኙነት ሂደቶች ላይ ለመወያየት ያለመ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ለወታደራዊ እና ለባሕር ንግድ አገልግሎት የሚውል የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከሶማሊላንድ ጋር በመፈራረም ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት መስማማቷን ታሕሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ማስታወቋ ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድ ዓመት ያክል የቆየ የከረረ ውዝግብ ውስጥ ገብተው መቆየታቸው ይታወቃል።
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ አለመግባባቶችን የፈጠረ ሲሆን፤ ሶማሊያ "ስምምነቱ ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው" ስትል ስትከስ ቆይታለች።
ይህም ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት በመፈጠሩ፤ ሞቃዲሾ አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ እንደምትጠራ እና የኢትዮጵያ ወታደሮችን ከአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ እንደምታስወጣ በመግለጽ፤ ከግብፅ እና ኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክራለች ቆይታለች።
ይህንንም ተከትሎ በታሕሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አደራዳሪነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን አለመግባባት ለማቆም የሚያስችል ውይይት በማድረግ የሀገራቱ መሪዎች ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
በዚህም ስምምነት ላይ የሁለቱን ሀገራት ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የግዛት አንድነትን ለማረጋገጥ ያለመና በመርህ ላይ የተመሰረተ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል።
በዚህም በአንካራው ስምምነት መሠረት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ዲፕሎማሲዊ መሻከር መሻሻል በማሳየቱን ተከትሎ፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጥር 3 ቀን 2017 በአዲስ አበባ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በዚህም ጉብኝት ሁለቱ መሪዎች በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ከውይይቱ በኃላ በሰጡት የጋራ መግለጫ "በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነትና ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም፤ ለቀጣናው መረጋጋት የጋራ መተማመን እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር ለማድረግ" መስማማታቸው ተነግሯል።
በተጨማሪም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስና ሀገራቱ በየመዲኖቻቸው ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና እንዲኖር ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን፤ "ቀጠናዊ ግንኙነቶችን ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እና የጋራ እድገትን ለማስቀጠል በትብብር ለመስራት" መስማማታቸውም ተነግሯል።
እንዲሁም በአንካራ ለተደረሰው የጋራ ስምምነትም በወዳጅነት እና በአጋርነት መንፈስ ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን በማረጋገጥ፤ በስምምነቱ የተቀመጡ የቴክኒክ ድርድሮች በፍጥነት እንዲጀመሩ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት የመጀመሪያው ዙር ቴክኒካዊ ድርድር የካቲት 11 ቀን 2017 በአንካራ የተካሄደ ሲሆን፤ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሁለቱን ሀገራት ልዑካን ቡድን በተናጠል እና በጋራ አነጋግረዋል፡፡
በዚህም ቴክኒካል ድርድር ሁለቱም ልዑካን የአንካራው ስምምነት መፈጸም ላይ ያላቸን ቁርጠኝነት ያሳዩበት መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ከቀናት በፊት የካቲት 14 ቀን 2017 በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ ልዑክ በሶማሊያ የሥራ ጉብኝት አድርጓል፡፡
በጉብኝቱም ልዑኩ ከሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ኃይሎች የመከላከያ ሰራዊት አዛዥ ሜጀር ጀነራል ኦዳዋ ዩሱፍ ራጌ ጋር በቀጣናው ስላለው የፀጥታ ሁኔታ ሀሳብ መለዋወጡ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የሚኖረውን ተሳትፎ በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሁለቱ ሃገራት በቱርክ አደራዳሪነት ውጥረትን ለማርገብ ከተስማሙ ወዲህ ሞቃዲሾ ሲገቡ የዛሬው ለመጀመሪያ ሲሆን፤ በጉብኝታቸውም አፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላትን ሚና በማጠናቀቅ እና በሶማሊላንድ ስምምነት ዙሪያ ያሉ ጥርጣሬዎችን ለመፍታት ትኩረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በጉብኝቱ ማጠናቀቂያ ላይ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ እና የጸጥታ ትብብር ቀጣይ እርምጃዎችን የሚገልጽ የጋራ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በእዮብ ውብነህ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ