Ahadu Radio And Television
February 27, 2025 at 12:51 PM
*ትራምፕ የአውሮፓ ኅብረት ምርቶች ላይ 25 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ አስታወቁ*
👉 "ኅብረት የተቋቋመው አሜሪካን ለመናድ ነው" ብለዋል
የካቲት 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ በተመረቱ ሸቀጦች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ ለመጣል ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የመጀመሪያውን የካቢኔ ስብሰባቸውን በዋይት ሀውስ ባካሄዱበት ወቅት ሲሆን፤ በሕብረቱ ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ "በቅርብ ጊዜ" እንደሚጣል አስታውቀዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከካናዳ እና ሜክሲኮ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ላይ የ25 በመቶው ቀረጥ ጥለው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ከሀገራቱ መሪዎች ጋር በድንበር ደህንነት ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ ቀረጡንን ማንሳታቸው ይታወሳል።
ነገር ግን ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ቀረጥ ጥለዋል።
ቻይናም በምላሹ 15 በመቶ በአሜሪካ የድንጋይ ከሰል እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ላይ እንዲሁም 10 በመቶ የአሜሪካ ድፍድፍ ዘይት፣ የእርሻ መሳሪያዎች እና አንዳንድ አውቶሞቢሎች ላይ ቀረጥ መጣሏን አስታውቃለች፡፡
ፕሬዝዳንቱ "በአውሮፓ ኅብረት ላይ ቀረጥ ስለመጣል ውሳኔ ተወስኗል ወይ?" ተብለው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ "ውሳኔ ወስደናል፡፡ በቅርቡ እናሳውቃለን" ብለዋል።
በአጠቃላይ በአውሮፓ ኅብረት ላይ የሚጣለው የ25 በመቶ ቀረጥ፤ በመኪናዎች እና በሌሎች ምርቶች ላይ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
"የአውሮፓ ኅብረት ከካናዳ የተለየ ጉዳይ ነው" ያሉት ትራምፕ፤ "ኅብረቱ በተለየ መንገድ ተጠቅሞብናል" ሲሉም ወቅሰዋል።
ይህንንም ሲያብራሩ "መኪኖቻችንን አይቀበሉም፣ መሠረታዊ የእርሻ ምርቶቻችንን አይቀበሉም፣ ለምን እንደማይፈልጉ ሁሉንም አይነት ምክንያቶች ይጠቀማሉ" ያሉ ሲሆን፤ "እኛ ሁሉንም ነገር ከእነሱ እንቀበላለን፣ እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም “የአውሮፓ ኅብረት የተቋቋመው አሜሪካን ለመናድ ነው።" ብለዋል
"እውነት እንነጋገር ከተባለ የአውሮፓ ኅብረት የተቋቋመው አሜሪካን የመናድ አላማ ይዞ ነው። በዚህም ጥሩ ሥራ ሰርተውበታል። አሁን ግን ፕሬዝዳንት ሆኛለሁ።" ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ ኅብረቱ ለውሳኔው 'አጸፋውን ሊመልስ' እንደሚቾል የጠቆሙም ሲሆን፤ ነገር ግን የተሳካ አጸፋ ሊሆን እንደማይችል በመግለጽ ሀገራቸው አሸናፊ እንደምትሆን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረቱ ቃል አቀባይ፤ "ኅብረቱ ከቀረጥ ጋር ተያይዞ ሕጋዊ ያልሆኑ እና አድሎአዊ ፖሊሲዎችን እንደሚቃወም ገልጸዋል።
አክለውም ፖሊሲዎቹ ጥቅም ላይ የሚውልበትን ጊዜ ጨምሮ፤ ለነፃ እና ፍትሃዊ ንግድ ፍትሃዊ ያልሆኑ እንቅፋቶች ላይ ኅብረቱ ጥብቅ እና ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
"የአውሮጳ ኅብረት በዓለም ትልቁ ነፃ ገበያ ነው" ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ለአሜሪካም ትልቅ ጥቅም ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ