
Ahadu Radio And Television
February 27, 2025 at 04:09 PM
*አባላቱ ሙሉ ነፃ አገልግሎት የሚያገኙበት የፌዴራል ፖሊስ ፋርማሲ በ1 ወር ውስጥ የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገለጸ*
የካቲት 20/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የተለያዩ መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሕበረሰቡ ማቅረብ ታሳቢ አድርጎ የተከፈተው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ፋርማሲ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራበት እንደሚገኝ ተገልጿል።
በሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት ዋና መምሪያ ጽህፈት ቤት እና የጥራትና ቁጥጥር ዋና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ናሆም ፀሀይ፤ ፋርማሲው በተለያዩ የጤና ዘርፉ አካላት ግምገማ ተካሂዶ እንዲሁም እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ታይቶና ተረጋግጦ አስፈላጊውን ደረጃ ያሟሉ መድኃኒቶች እንዲገቡ ተደርጎ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሚቀረው የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት ብቻ ሲሆን፤ ተጨማሪ የሰው ሀይልን በመቅጠር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንዲገባ እየተሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አያይዘውም ተጨማሪ መድኃኒቶችን ለመጠቀም በብዙ ሚሊዮን ብር ውል መገባቱን በማንሳት፤ ጊዜያቸውን እየጠበቁ ወደ ፋርማሲው የማስገባት ሥራ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
"የሽያጭና ግዢ ስርዓቱም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በኮምፒውተር እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራበት ይገኛል" ብለዋል።
የፖሊስ አባላት ሙሉ ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንደሚያገኝ ያስታወሱት ኃላፊው፤ ከዚህ ቀደም ታካሚዎች በሆስፒታሉ ውስጥ የማይገኙ መድኃኒቶችን ከውጪ ውል ከተፈጸመባቸውና በአዲስአበባ መስተዳድር ሥር ከሚገኙ ፋርማሲዎች ከገዙ በኋላ ሂሳብ የሚወራረድበት አካሄድ ስለመኖሩ ጠቁመዋል።
በመሆኑም እነዚህ መድኃኒት ቤቶች በርቀት ስለሚገኙ በዋናነት የፖሊስ አባላት ወደሌላ ቦታ በመሄድ እንዳይንገላቱ በማድረግ እዛው የፖሊስ ሆስፒታል ውስጥ እንዲገለገሉ ለማስቻልና ሕብረተሰቡንም ተጠቃሚ ለማድረግ ሲባል፤ ከመንግሥት የግዢ ስርዓት ሳይዛባ በቀላሉና በተሻለ መድኃኒትን ማግኘት በሚቻልበት አግባብ መከፈቱን ተናግረዋል።
ሌሎች ላይ ቢኖርም ግን እንደ ኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል የመጀመሪያው የማሕበረሰብ ፋርማሲ በመሆኑ፤ ሠራተኞችን ከመጥቀምና ተቋሙ ራሱን አሳድጎ ገንዘብ ማግኘት የሚችልበትን መንገድ ከመፍጠር አንፃር በሥራ ሂደት እንደ አዲስ እየተሻሻሉ የሚሄዱ መመሪያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
"እነዚህ መመሪያዎች እየታደሱ ሲሄዱ የ24 ሰዓትንና ሌሎች አገልግሎቶችን ጨምሮ የተሻለ ደረጃ ማድረስ ይቻላል" ሲሉም ተናግረዋል።
ልደታ በሚገኘው የፖሊስ ሆስፒታል ውስጥ ያለው ፋርማሲው ጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል።
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
