
Ahadu Radio And Television
February 28, 2025 at 07:46 AM
*ለሜዲካል ኢንቨስትመንት ትኩረት ባለመሰጠቱ በሚፈለገው ልክ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም ተባለ*
የካቲት 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የተለያዩ ፖሊሲዎች ቢጸድቁና ለመድኃኒት አምራች ማኅበራት የማምረቻ ቦታዎች ቢመቻችም የሜዲካል ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት ተሰቶ ካልተሰራ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ እንደ ሀገር ያሉት የመድኃኒት አምራች ማኅበራት ቁጥር ካለው የመድኃኒት እና የሕክምና ግብዓት ምርት ፍላጎት አንጻር በቂ ምርት አለመኖሩን ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ አምራች ማኅበራት የተመረቱ የመድኃኒት እና የሕክምና ግብዓት በሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይገደቡ የዓለም አቀፍ ምዘናን አሟልተው ለውጭ ሀገር ገበያ እንዲቀርቡ ለማስቻል በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አክለውም የማኅበራቱን የማምረት አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ ሕጎች እንዲሁም ፖሊሲዎች ቢቀየሩም፣ ለዘርፉ አምራች ማኅበራት መድኃኒት የማምረቻ ቦታዎች ቢዘጋጁም በተፈለገው መጠን ለውጥ ሊመጣ አለመቻሉን ሚኒስቴር ዲኤታዋ ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሃብቶች ወደ ሀገር በመግባት በማምረት የሥራ ሂደት ሲሳተፉ ለሚያነሱት ጥያቄዎች የሚሰጡ ምላሾች በተመለከተ እንዴት ሊመለስ ይችላል? የሚለውን በተመለከተ፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግምገማ መከናወኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተከናወነው የምልከታ ሂደት ወቅት ከታዩ ጉድለቶችን መካከል ለኢንቨስተሮች አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በማጋራት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸው ተጠቃሽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አክለውም "በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘርፉን በሚመለከት የተቀመጡ ፖሊሲዎች ግልጽ ቢሆኑም፤ ለኢንቨስተሮች የማስረዳት ሂደት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው" ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ፤ ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የመድኃት ምርት በተመለከተ በኢትዮጲያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የክትትል እና የምርት ደረጃ ቁጥጥር የሚካሄድበት አሰራር ስለመኖሩም ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
መድኃኒት የሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ መሆኑን የሚያነሱት ሚኒስትር ዲኤታዋ፤ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ተብለው ተለይተው እንዲሁም የሚያስፈልጉ ድጋፎች በተመለከተ ሊሰራባቸው የሚገቡ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
የሜዲካል ኢንቨስትመንት በተመለከተ የሚመለከተው አንድን ተቋም ብቻ ሳይሆን፤ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለሜዲካል ኢንቨስትመንት ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነውን መድኃኒት ከውጭ ታስገባለች፡፡
በሀገር ውስጥ ያለው የመድኃኒት ገበያ በዓመት ከ400 እስከ 500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያህል እንደሚደርስና ዓመታዊ ዕድገቱም 25 በመቶ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
