
Ahadu Radio And Television
February 28, 2025 at 01:45 PM
*ለስደተኞች የሚደረገው ዓለም አቀፍ ድጋፍ መቀነሱ ፈተና እንደሆነበት የስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት ኤጀንሲ ገለጸ*
የካቲት 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከተለያዩ የጎረቤት ሀገራት ፈልሰው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች እየተደረገ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነሱ እንቅፋት እንደሆነበት የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
የአገልግሎቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በአካል ንጉሤ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን እና የሌሎች ሀገራት ጥገኝነት ጠያቂ ዜጎች በኢትዮጵያ መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን በአማራ ክልል መተማ አካባቢ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉምሩክ አካባቢ በተዘጋጁ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙት ፍልሰተኞች እንዲውል ይደረግ የነበረው ዓለም አቀፍ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመሆኑ፤ ለስደተኞቹ መሟላት የሚገባቸውን መሰረታዊ ነገሮች ለማሟላት እንቅፋት እየሆነ ይገኛል።
ይህም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፉ መቀዛቀዝ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ፤ ለጋሽ ሀገራትና ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ አገልገሎት ኤጀንሲ ያጋጠመውን የድጋፍ ጉድለት ለማቃለል ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም ኃላፊዋ ነግረውናል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጥበቃ ለሚሹ ጥገኝነት ጠያቂዎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የስደተኞች አዋጅ ቁጥር 1110/2011 እንዲሁም አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና መርሆዎች መሠረት አጋር አካላትን እያስተባበረ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከ26 ሀገራት ከለላና ጥበቃ ፈልገው ለመጡ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላና ጥበቃ እየሰጠች እንደምትገኝ ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በፅዮን ይልማ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
