Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
February 28, 2025 at 01:46 PM
*ኮሚሽኑ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከሰሞኑን የተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገለጸ* የካቲት 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በዜጎች ላይ ተፈጸሙ በተባሉ ግድያዎችና ጥቃቶች ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጿል። በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህርዳር የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሕክምና ክፍል ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር አንዱአለም ዳኜ ጥር 24/2017 ዓ.ም መገደላቸው ይታወሳል። በተመሳሳይም በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጌራ ወረዳ ዋላ በተባለ ቀበሌ የካቲት 6/2017 ዓ.ም. አቶ ዛኪር አባ ኦሊ የተባሉ ባለሀብት መገደላቸውን ተከትሎ የነዋሪዎች ቤትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ለአሐዱ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚደርሰው ጥቆማም አሊያም በራሱ ተነሳሽነት ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን አክለው ገልጸዋል። በተያያዘም ኢሰመኮ በሩብ ዓመቱ ባወጣው ሪፖርት ከፍርድ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የንጹሃን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ናቸው ብሏል። በተጨማሪም የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀል እና የዳኝነት ነጻነት መሸርሸር ይገኙበታል ሲል ገልጿል። በፍርቱና ወልደአብ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *ኮሚሽኑ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከሰሞኑን የተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገለጸ*   የካቲት...

Comments