
Ahadu Radio And Television
February 28, 2025 at 04:14 PM
*በዘንድሮው የሃጅ ጉዞ ባለፈው ዓመት የተፈጠሩ ክፍተቶች እንዳይኖሩ ሥራዎችን መስራቱን የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ*
የካቲት 21/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዘንድሮ በሚደረገው የሃጅ ጉዞ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያውያን ሃጅ ተጓዞች ላይ የተፈጠሩ ጉዳቶችና ሞቶችን እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ሥራዎችን መስራቱን ገልጿል።
ባለፈው ዓመት በተደረገው ለሃጅ ጉዞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀኑ አምስት ኢትዮጵያውያን በሕመም እና በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን እንዳጡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጹ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት በተደረገው የሃጅ ጉዞ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሺሕ 300 በላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ሟቾች ያለፈቃድ ወደ አገሪቱ ገብተው በከፍተኛ ሙቀት ረጅም ርቀት የተጓዙ ምዕመናን እንደሆኑ ተገልጿል።
ከሟቾቹ ውስጥ ከሦስት አራተኛ በላይ ፍቃድ ሳይኖራቸው የገቡ እና በቂ መጠለያ ሳይኖራቸው በጠራራ በፀሐይ ሲጓዙ የነበረ ሲሆን፤ ከሞቱት መካከል አንዳንዶቹ አረጋውያን ወይም ሥር የሰደደ ሕመም የነበረባቸው ናቸው ተብሏል።
በዚህም "በዘንድሮው ጉዞ ይህን መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን አይነት የጥንቃቄ እርምጃዎች ተወስደዋል?" ሲል አሐዱ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ጠይቋል።
በምክር ቤቱ የሃጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አብዱልፈታህ መሀመድ በክልሎች እና በሌሎች መመዝገቢያ ቅርንጫፎች ለሃጅ ጉዞ የሚመጡ ተመዝጋቢዎች በእድሜ የገፉ ከሆኑ ያለ አጋዥ እንዳይመዘገቡ ማድረግን ጨምሮ የክትትል ሥራዎችን እየተሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ በሕመም የቆዩ ተመዝጋቢዎች አጋዥ እንዲኖራቸውና አጋዥ ይዘውም ጉዞው ለአደጋ የሚያጋልጣቸው ተጓዞች እንዳይመዘገቡ እየተደረገ መሆኑ አንስተዋል።
"ምክር ቤቱ ከባለፈው ዓመት ትምህርቶችን በመውሰድ የጥንቃቄ ሥራዎችን በስፋት ሰርቷል" ሲሉም አክለዋል።
በተያያዘም የሃጅ ተጓዞች በዘንድሮው የሃጅ ጉዞ የሚጓዙ አርሶ አደሮች ለጉዞ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የሚያዘጋጁት ብር ከውጭ ምንዛሬ ጋር ያለመጣጣም ችግር ገጥሞት እንደነበር ገልጸዋል።
ለዚህም አርሶ አደሮች እህል ሽጠው የሚያመጡት የገንዘብ መጠን እና የሃጅ ክፍያ መጨመር ችግር በተወሰነ መልኩ እንደበር አንስተዋል።
"ባለፉት አምስት ቀናት ግን የእህሉ የሽያጭ የተሻሻለ መሆኑ ችግሩን በተወሰነ መልኩ ሊቀረፍ ችሏል" ብለዋል።
የዘንድሮ የሃጅ ጉዞ ምዝገባ ከጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም የጀመረው ምዝገባ ዛሬ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል።
በዘንድሮው የሃጅ ጉዞ ለ10 ሺሕ ተጓዦች መፈቀዱ ይታወቃል።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ