Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
March 1, 2025 at 08:48 AM
*የትራምፕ እና የዜለንስኪ የዋይት ሃውስ ውይይት የከረሩ ንግግሮች ተስተናግደውበት ያለምንም ስምምነት ተቋረጠ* 👉 ትራምፕ ዘለንስኪን "በሚሊየኖች ሕይወትና በ3ኛ የዓለም ጦርት ቁማር እየተጫወትክ ነው" ሲሉ ከሰዋል የካቲት 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በትናንትናው ዕለት በዋይት ሃውስ ያደረጉት ውይይት የከረሩ የቃላት ልውውጦች ተስተናግደውበት ያለምንም ስምምነት ተቋርጧል። ዘለንስኪ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር፤ "ኦቫል ኦፊስ" በተሰኘው የፕሬዝደንቱ ጽሕፈት ቤት ውስጥ በትናንትናው ዕለት የተጋጋሉ ንግግሮች የተሞላበት ውይይት አድርገዋል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር አወንታዊ ውይይት በማድረግ አሜሪካ ከዩክሬን ልዩ ማዕድናት ማግኘት የሚያስችላት ስምምነት ለመፈረም፤ በዚህም "ከአሜሪካ ቀጥተኛ የደህንነት ዋስትና" የማግኘት ተስፋን ሰንቀው ነበር ወደ አሜሪካ ያቀኑት፡፡ ነገር ግን በምትኩ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት፤ ወደ ጦፈ ክርክር እና የቃላት ግጭት አምርቶ ምንም ስምምነት ሳይደረስበት ተቋርጧል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ለዓመታት አሜሪካ ለዩክሬን ላደረገችው ድጋፍ 'እንዲያመሰግኑ' ዘለንስኪን የጠየቁ ሲሆን፤ ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በዓለም ሚዲያ ፊት 'ያልተለመደ አለባበስ' ለብሰው በመገኘታቸውም በመድረኩ ኮንነዋቸዋል። ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያው ፕሬዝዳን ቭላድሚር ፑቲን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው ደጋግመው ያሳሰቡት ትራምፕ እና ምክትላቸው፤ የዘለንስኪ ምላሽ "አክብሮት የጎደለው ነው" ሲሉም ወቅሰዋቸዋል። ዘለንስኪ "የሰላም ስምምነት ለመፈረም ዋስትና ያስፈልገናል" ያሉ ሲሆን፤ ትራምፕ በበኩላቸው "ለመደራደሪያ የሚሆን አቅም እና ሥልጣን የለህም" በማለት የፕሬዝዳንቱን ንግግር በድንገት አቋርጠዋል፡፡ ትራምፕ አክለውም "ያለህ አማራጭ ስምምነቱን መፈረም ነው ካልሆነ አሜሪካ ከዚህ ትወጣለች" ሲሉ አሳስበዋል። በውይይቱ የመጀመሪያ ጥቂት ደቂቃዎች ላይ መልካም የሚመስሉ ንግግሮች የተስተዋሉ ቢሆንም፣ ነገር ግን የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ "የሰላም መንገድ እና የብልጽግና መንገድ በዲፕሎማሲ ውስጥ እያለፈ ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው።" ማለታቸውን ተከትሎ፤ በኦቫል ቢሮ ውስጥ የነበረው የውይይት መንፈስ ወደ ውጥረት እና የከረረ ንግግር ማምራት ጀምሯል። በዚህ ወቅትም ዘለንስኪ ሩሲያ ሙሉ ወረራ ከመጀመሯ ከሦስት ዓመታት በፊት በፊት ባሉት ዓመታት ያደረሰችውን ጥቃት በመጥቀስ፤ እ.ኤ.አ. በ2019 ያልተሳካ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም "ማንም አላስቆመውም" ሲሉ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል። ዘለንስኪ አክለውም "ምን አይነት ዲፕሎማሲ ነው ጄዲ የምታወራው? ምን ማለትህ ነው?" በማለት ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ጥያቄ ሰንዝረዋል። ቫንስ ሲመልሱም "የአገራችሁን ጥፋት የሚያቆመው ዓይነት" ማለታቸውን ተከትሎ፤ ውይይቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ክርክር እና ውጥረት ተቀይሯል፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ዘሌንስኪን በአሜሪካ ሚዲያ ፊት ለፊት ያሳዩት ባህሪ አክብሮት የጎደለው እና "ሙግት" የተሞላበት ነው በማለት ከሰዋል። ይህንን ተከትሎም ቫንስ በውትድርና እና በውትድርና አገልግሎት ላይ ባጋጠመው ችግሮችን አንስተው፤ ለዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ዜለንስኪም በምላሻቸው "በጦርነቱ ወቅት ሁሉም ሰው ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። እርሶም ቢሆኑ፡፡ ግን ጥሩ ውቅያኖስ አለዎት እና አሁን አይሰማዎትም፣ ግን ለወደፊቱ ይሰማዎታል" ሲሉ ተናግረዋል። ይህም የዘለንስኪ አስተያየት በዜለንስኪ እና በምክትል ፕሬዝዳንቱ ብቻ ተወስኖ የነበረው ሙግት ላይ ትራምፕ እንዲሳተፉበት ያስገደደ ሲሆን፤ ይህም የትራምፕን ትልቁን የቁጣ ምላሽ ቀስቅሷል። "ምን እንደሚሰማን አትንገረን! ይህን ለመምከር ምንም አይነት አቋም የለህም" ሲሉም ዶናልድ ትራምፕ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለዘለንስኪ አስተያየት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ "አሁን ካርዶቹ የሉህም" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ፤ "በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ቁማር ትጫወታለህ" ሲሉም ዘለንስኪን ወቅሰዋቸዋል፡፡ በዚህ ወቅት የዩክሬን መሪ ትራምፕ ከጦርነቱ አጥቂ ጋር የመገናኘትን የሞራል አደጋ ሊረዱ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል። በውይይቱ ላይ ዘለንስኪ "ከጦርነቱ መጀመሪያ ጀምሮ ብቻችንን ነበርን እና አመስጋኞች ነን" ማለታቸውን ተከትሎም፤ ይህ ንግግር ዳግም ትራምፕን አስቆጥቷል፡፡ "ብቻህን አልነበርክም። በዚህ ደደብ ፕሬዝዳንት በኩል 350 ቢሊዮን ዶላር ሰጠንህ" ሲሉ ትራምፕ፤ የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳን ጆ ባይደን ማጣቀሻ አድርገዋል። ከዚያም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዜለንስኪ አሜሪካን አመስግነው እንደሚያውቁ የጠየቁ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ በተካሄደው ምርጫ ወቅትም "ለተቃዋሚዎች" ወይንም ለዴሞክራቶች ዘመቻ አድርገዋል ሲሉ ከሰዋል። ትራምፕ "አታሸንፍም ይህን እያሸነፍክ አይደለም" ሲሉም ዘለንስኪን የተናገሩ ሲሆን፤ "በእኛ ምክንያት ግን ከችግር የመውጣት በጣም ጥሩ እድል አለህ።" ብለዋል፡፡ ውይይቱ ወደተጋጋለ ንግግር መሸጋገሩን ተከትሎም "እንዲህ አይነት ውይይት ማድረግ በጣም ከባድ ነገር ይሆናል" ያሉት ትራምፕ፤ "አመለካከቶቹ መለወጥ ስላለባቸው ይህን ለማድረግ ከባድ ስምምነት ይሆናል" ብለዋል፡፡ በዚህ በክርክር እና መደማመጥ በጎደለበት የዋሽንግተን ውይይት ላይ፤ በአሜሪካ የዬክሬን አምባሳደር ኦክሳና ማርካሮቫ እጆቻቸውን ጭንቅላታቸውን በላይ ጭነው በጭቅጭቅ ውስጥ ሆነው ታይተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት እና ትራምፕ ለታቀደለት የዜና ኮንፈረንስ ወደ መድረክ ከመውጣታቸው በፊት፤ ዘለንስኪ በመጨረሻ ዋይት ሃውስን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። ዘለንስኪ ውይይቱን አቋርጠው በመኪና ከመውጣታቸው ጥቂት ቀደም ብሎም ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ፤ "ለሰላም ስትዘጋጁ ተመለሱ" ሲል ጽፈዋል። "ስምምነቱ ተዘርዟል" ሲሉም አስታውቀዋል። "የአሜሪካ ተሳትፎ የሚቀጥል ከሆነ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ለሰላም ዝግጁ እንደማይሆን ገንዝቤያለሁ። ምክንያቱም የኛ ተሳትፎ ለድርድር ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጠው ያምናል" ብለዋል ትራምፕ በጽሁፋቸው። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ኤክስ በተሰኘው የማኅበራዊ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ "አመሰግናለሁ አሜሪካ" ያሉ ሲሆን፤ " የአሜሬካ ፕሬዝደንት፣ የምክር ቤት አባላትንና የአሜሪካን ሕዝብ እናመሰግናለን። ዩክሬን ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም ትፈልጋለች፣ ያንን ለማግኘትም በሚገባ እየሠራን ነው" ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት በዚህ ሳምንት በሁለቱ ወገኖች መካከል ይደረጋል ተብሎ የተጠበቀው እና በብዙሃን ዘንድ ሙገሳን አግኝቶ የቆየው የማዕድን ድርድር በሁለቱ መሪዎች መካከል በተፈጠረው ከፍተኛ ውዝግብ ምክንያት ሳይፈረም ቀርቷል። በእዮብ ውብነህ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com

Comments