
Ahadu Radio And Television
March 1, 2025 at 08:49 AM
*"የዓድዋ ድል በዓልና የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ሰፊ ቁርኝት አላቸው" ፕሮፌሰር አንዱአለም ደነቀ*
የካቲት 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዛሬው ዕለት ለ52ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 179 የሕክምና ተማሪዎችን አስመርቋል።
በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርስቲው ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አንዱአለም ደነቀለ የዓድዋ ድል በዓል እና ኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ሰፊ ቁርኝት አላቸው ሲሉ ገልጸዋል።
የዛሬ 129 ዓመት ኢትዮጵያ አንድም ዘመናዊ ሀኪም የጤና ባለሙያ ስላልነበራት ለጦርነት ሲሄዱ የተከተላቸው የሕክምና ባለሙያ እንዳልነበረ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ወቅትም የጦር ጉዳተኞችን የሚያክሙ ከሩሲያ ቀይ መስቀል የመጡ የሕክምና ባለሙያዎች እንደነበሩ አንስተዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሆስፒታል ዳግማዊ ሚኒሊክ ሊቋቋም መቻሉን በመግለጽ፤ "ከዛ በኋላ በርካታ የሕክምና ትምህርት ቤቶች መቋቋም በመቻላቸው ብቻ በዛሬው ዕለት በአንድ የሕክምና ትምህርት ቤት ብቻ በርካታ ሀኪሞችን ማስመረቅ ችለናል" ብለዋል።
በኮሌጁ የመውጫ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ 94 ነጥብ 4 በመቶ ማለፋቸውን የተናገሩት ፕሮፌሰር አንዱአለም፤ የተገኘው ውጤት ትልቅ ቢሆንም ግን በቂ ነው ተብሎ እንደማይታሰብ በመግለጽ ሁሉም ማለፍ እንደነበረባቸው አንስተዋል።
በመሆኑም ሁሉም ተማሪዎች እንዲያልፉና የተሻለ ውጤት እንዲያገኙ ለማድረግ በተማሪዎችና ባለሙያዎች ላይ ተጨማሪ ሥራን እንደሚጠይቅ ያሳሰቡ ሲሆን፤ "ወደፊት የሚወጣው ፈተናም እየከበደ እንጂ እየቀለለ ስለማይሄድ ሁላችንም መጠንከር አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ "አድዋ ሀገራችንን ሊወር የመጣውን ጠላት ድል ያደረግንበት ጊዜ ነው" ብለዋል።
ይህ ምርቃት ተማሪዎች እውቀት የጨረሱበት ሳይሆን ከወጡ በኋላም ነገ በተግባር የሥራ ባህልን የሚያሳድሩበትና የኅብረተሰቡን ባህል በመረዳት በቅንነት ማስተናገድ እንደሚገባቸው በመጥቀስ፤ "ሕሙማኑን ከልባችሁ ለማገልገል የገባችሁትን ቃለመሃላ ሁሌም ልታስቡት ይገባል" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎትም ወደላቀ ደረጃ ያሳድጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ ለተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ተማሪዎች ወደሥራ ዓለም ሲሰማሩ ሕዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይም በዘንድሮው ዓመት በአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፍተኛውን ውጤት ያመጣችው ተመራቂ ኤልሳቤጥ አርአያ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆናለች።
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ