Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
March 1, 2025 at 10:07 AM
*ለልማት በሚል ተማሪዎች በየወሩ 500 ብር እንዲከፍሉ መደረጉ አግባብ አደለም ሲሉ የተማሪ ወላጆች ቅሬታ አቀረቡ* የካቲት 22/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ጸሐይ ጮራ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ ለልማት እና ለሕጻናት ማቆያ በሚል እስከ 5 መቶ ብር እየተጠየቁ መሆኑን የተማሪ ወላጆች ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ተጽእኖ እያሳደረባቸው እንደሚገኝ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ "መክፈል የማይችሉ ወላጆችና ተማሪዎች በአስገዳጅነት እንዲከፍሉ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡ አክለውም "ይሰራል የሚባለው የሕጻናት ማቆያም ቢሆን ምንም አይነት ጅምር ሥራ የለም" ያሉ ሲሆን፤ ክፍያውን ያለደረሰኝ በአስገዳጅነት እንደሚያስከፍሉም አንስተዋል፡፡ ያለአግባብ ከሚፈጸመው ክፍያ በተጨማሪ "በትምህርት ቤት ውስጥ ከመጸዳጃ የሚወጣ ፍሳሽ በአግባቡ ባለመወገዱ በተማሪዎች ላይ የጤና ችግር እያስከተለ በመሆኑ፤ ጉዳዩን ትምህርት ቤቱ ትኩረት አልሰጠውም" ሲሉ ቅሬታቸውን አክለዉ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ይህ ቆሻሻ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ የሚያልፍ በመሆኑ፤ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ችግሩ እንዲወገድ የሚመለከተውን አካል ቢያነጋግሩም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡ አሐዱም ቅሬታዉን ተቀብሎ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ጸሐይ ጮራ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ታሪኩ ደሳለኝን አነጋግሯል፡፡ ርዕሰ መምህሩ በምላሻቸውም "ከፍሳሹ ጋር ተያይዞ የተነሳው ቅሬታ ከእውነት የራቀ እና ሆን ተብሎ የትምህርት ቤቱን ሥም ለማጥፋት የታሰበ ነው" ብለው፤ ከክፍያ ጋር በተያያዘ የተነሳው አቤቱታ ከወላጅ ኮሚቴ ጋር በመሆን እስከ 500 ሺሕ ብር የውስጥ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ የተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህም ደግሞ የወላጅ ኮሚቴው እና የሚመለከተው አካል በጋራ በመሆን ስምምነት መደረጉን አንስተው፤ ምንም ያለደረሰኝ የፈጸመ ክፍያ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ጋርም ሆነ ከክፍያዉ ጋር በተያያዘ በትምህርት ቤቱ እየተከናወነ ያለው ተግባር "ከሕግ ውጭ ነው" ቢሉም፤ ርዕሰ መምህሩ በበኩላቸው "ውንጀላው ከእውነት የራቀ ነው" ብለዋል፡፡ አክለወሰም የሚስተካከሉ ክፍተቶች ቢኖሩም በውይይት መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በአለምነው ሹሙ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *ለልማት በሚል ተማሪዎች በየወሩ 500 ብር እንዲከፍሉ መደረጉ አግባብ አደለም ሲሉ የተማሪ ወላጆች ቅሬታ አቀረ...

Comments