Addis Ababa Education Bureau
Addis Ababa Education Bureau
February 17, 2025 at 12:53 PM
ከርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ጋር ለሚደረግ የስራ ውል ስምምነት በተዘጋጀ ረቂቅ ሰነድ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ። (የካቲት 10/2017 ዓ.ም) በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ የክፍለ ከተማና ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ፣ሱፐርቫይዘሮች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ርዕሳነ መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ረቂቅ ሰነዱ የትምህርት አመራሩ የመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ቢሮው በየደረጃው ከሚገኙ ርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ጋር ለ3 አመት የሚቆይ የስራ ውል ስምምነት ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልጸው በስምምነት ሰነዱ መሰረት አፈጻጸማቸው የላቀ ለሆኑ አመራሮች ዕውቅና በመስጠት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ የትምህርት አመራሮች በውሉ በተቀመጠው መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል። ዶክተር ዘላለም አያይዘውም ቢሮው እንደውል ሰጪ ተቋም በየትምህርት ተቋማቱ ያለውን አፈጻጸም በሚያደርገው ድጋፍና ክትትል የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸው በዛሬው ውይይት በረቂቅ ሰነዱ ዙሪያ የሚጨመሩ የማስተካከያ ሀሳቦች ተካተው ሰነዱን ተግባራዊ ወደማድረግ ስራ እንደሚገባ አመላክተዋል። በውል ስምምነቱ መሰረት የተማሪዎችን ውጤት በተለይም የ6ኛ ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል፣ የተማሪዎችን እና የመምህራንን ስነምግባር ማሻሻል፣የተቋሙን ደረጃ ማሻሻል እንዲሁም የትምህርት ብክነትን መቀነስ ከርዕሳነ መምህራን የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር ረቂቅ ሰነዱን ባቀረቡበት ወቅት ገልጸው ሱፐርቫይዘሮችም በየክላስተራቸው በሚያደርጉት ድጋፍና ክትትል የሚያገኙትን ግኝት መሰረት በማድረግ ትምህርት ቤቶችን ማብቃት እንደሚገባቸው በውል ስምምነት ሰነዱ መቀመጡን አስታውቀዋል። ትምህርት ቢሮ የትምህርት አመራሩን የአመራር ብቃት በማሳደግ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል የሚያከናውነው ተግባር የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ የክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚ አዲሱ ሻንቆ (ዶ/ር) ገልጸዋል። ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች https://linktr.ee/aacaebc

Comments