
Addis Ababa Education Bureau
February 18, 2025 at 01:44 PM
የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሚያስፈትኑ የግል ትምህርት ቤቶች ጋር የፈተና ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት ተካሄደ::
(የካቲት 11/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሚያስፈትኑ የግል ትምህርት ቤቶች ጋር የበይነ መረብ ፈተና አሰጣጥ ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት አካሄዳል::
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ የ12ኛ ክፍል ፈተና ማስፈፀሚያ እቅድ ለተሳታፊዎች ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ውይይቱ ከ2016 ዓ.ም ልምድ በመቅሰም ችግሮችንና አሉታዊ ጎኖችን በመለየት ቀልጣፋና የአሰራር ስርዓቱ በአግባቡ የተዘረጋ የኦንላይን ፈተና ለመስጠት ያስችላል ብለዋል::
ቢሮው በ2017 ዓ.ም የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሳካ እንዲሆን ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት እየሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ሳምሶን የፈተና ግብአቶችን በመሰብሰብና በማደራጀት ፈተናውን ማከናወን እንዲችሉና ለኦንላይን ፈተናው እንዲዘጋጁ ቀድሞ ማቀድ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ::
የኦንላይን ፈተናው በ2016 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሰጠቱ ጋር ተያይዞ የታዩ እጥረቶች በዚህ ዓመትም ፈተናው በኦንላይን የሚሰጥ በመሆኑ ካለፈው ተሞክሮ በመውሰድ ቢሮው ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለጹት የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ዑመር ተማሪዎችም በተግባርና በስነልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ በጥንካሬ መስራት ከሁሉም አካላት ይጠበቃል ብለዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ በበኩላቸው ቢሮው ፈተናውን በበቂ ዝግጅት በተሻለ አፈፃፀም ለማስፈተን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ያለውን ሰፊ ጊዜ በመጠቀም ባለን ግብዓት በቂ ልምምድ በማድረግ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና የተሳካ ፈተና ለመፈተን የሚመለከተን አካላት ዝግጁ መሆን አለብን ሲሉ ተናግረዋል::
በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች በተፈጥሮ ሳይንስና ማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት አይነቶች 50, 807 ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ::
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/aacaebc