Addis Ababa Education Bureau
Addis Ababa Education Bureau
February 25, 2025 at 02:55 PM
የልደታ ክፍለ ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት 10ኛውን የመምህራን እና የተማሪዎች ስፖርት ሊግ ውድድር በድምቀት አስጀመረ። (የካቲት 18/2017 ዓ.ም) የልደታ ክፍለ ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት የ2017 ዓ.ም አመታዊ የስፖርት ሊግ ውድድር መክፈቻ መርሃ ግብር አካሂዷል:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ በስፖርት ሊግ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት የ2017 ዓ.ም የተማሪና መምህራን ስፖርታዊ ውድድር በሁሉም ክፍለ ከተሞች መካሄድ መጀመሩን አስታውሰው በአካልና በአእምሮ የዳበረ ትውልድ መፍጠር ለሀገር ብልፅግናና እድገት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል:: አክለውም ውድድሩ የራሱ አላማና ግብ ያለው ትውልድና ተተኪ ስፖርተኛ የሚፈራበት በመሆኑ ስፖርታዊ ውድድሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቢሮው ከፍተኛ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ባለድርሻ አካላት ለስፖርታዊ ውድድሩ ውጤታማነት በጋራ እንዲሰሩና ተወዳዳሪዎች ውድድሩን በጤናማ የፍክክር መንፈስ እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል:: የልደታ ክፍለ ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ ግርማ በበኩላቸዉ ስፖርት ፍቅርና መተሳሳብ የሚፈጥር እንዲሁም ብቁ የአካል ብቃት ያለው ትውልድ የሚፈጥር መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በውድድሩ 16 አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚደረጉ ጠቁመው ተወዳዳሪዎች የሚያገኙትን ውጤት በፀጋ በመቀበል በአንድነትና መተሳሰብ ወንድማማችነታቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል:: በክፍለ ከተማው የተጀመረው ስፖርት ሊግ ውድድር "የትምህርት ቤቶች ስፖርት ሊግ ውድድርን ባህል በማድረግ ጤናማ ንቁና ብቁ ትውልድ እንፈጥራለን!" በሚል መሪ ቃል ለተከታታይ አስር ቀናት የሚደረግ ሲሆን በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ ትምህርት ቤቶች በከተማ ደረጃ ለሚደረግ የስፖርት ሊግ ማጠቃለያ ውድድር የሚቀርቡ መሆኑ ተጠቅሳል:: በመክፈቻ መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ የክ/ከተማው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ ግርማ ፣ የክፍለ ከተማው ብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍቱ ብርሀኑ ተማሪዎችና መምህራን ተገኝተዋል:: ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች https://linktr.ee/aacaebc

Comments