
Addis Ababa Education Bureau
February 27, 2025 at 02:00 PM
የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት መደበኛ መርሃ ግብር ክትትልና ድጋፍ ግብረ መልስ ላይ ውይይት ተካሄደ::
(የካቲት 20/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርት የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርትና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ትግበራ ዳይሬክቶሬት በ11ዱ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ናሙና ጣቢያዎች የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት መደበኛ መርሃ ግብር አተገባበር ላይ የ 2017 ዓ.ም የ2ኛ ሩብ ዓመት ክትትልና ድጋፍ የተጠመረ ግብረመልስ ላይ ውይይት ተደረገ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ዑመር በውይይቱ ላይ እንዳሉት ቀደም ሲል በተደረገ ድጋፍና ክትትል ውጤት መሰረት በውጤቱ ላይ መወያየት በጥንካሬ የታዩትን ለማስቀጠልና ጉድለት ያሳዩት ሥራዎች ላይ ደግሞ የበለጠ በመስራት ልዩነቶችን ለማጥበብ እና ተቀራራቢ አፈፃፀም ላይ ለመድረስ አቅም ይፈጥራል ብለዋል::
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለዉም ከጎልማሶች ትምህርት ጋር በተያያዘ በክረምት ዘመቻ በርካታ ተማሪዎች የትምህርት እድሉን ያገኙና የብርሃን ምዘና መውሰዳቸውን ያብራሩ ሲሆን ከምዘናው በሃላ በ11 ዱ ክፍለ ከተሞች ካሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በየሙያ ዘርፉ ስልጠና እንዲወስዱ የተለዩ መሆናቸውን እና በቅርቡ የስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል ::
የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርት የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርትና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ ፈቃዱ በበኩላቸው ድጋፍና ክትትልሉ በ11ዱ ክፍለ ከተሞች የጎልማሶች ትምህርትን አስመልክቶ ለናሙናነት በተመረጡ 99 ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ትምህርትን በተመለከተ 75 ትምህርት ቤቶች ላይ 44 የቢሮ እና ክፍለ ከተማ ባለሙያዎችን በማሳተፍ መካሄዱን አስታውሰው የድጋፍና ክትትል ውጤቱ ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ ከመሥራት አንፃር ለማየት ያስቻለ ነው ብለዋል::
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በጎልማሶች ትምህርትን ውጤታማ ለማድረግም ሆነ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ከሌሎች እኩል ዕድል ከመስጠት እና የተለየ ድጋፍ ከማድረግ አንፃር አተገባበሩን መገምገምና ማሻሻል ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ በመሆኑ ትኩረት ሰጥታችሁ መስራት ይገባችኅል በማለት አሳስበዋል::
የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት የተጠመረ ግብረመልስ በአቶ ጌታቸው በላይነህ እንዲሁም የልዩ ፍላጎት የተጠመረ ግብረ መልስ በአቶ ፀጋዬ ሁንዴ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል ::
በውይይቱ የክፍለ ከተማ አስተባባሪዎች ፣ የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች የሁለቱም ዘርፎች ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የጣቢያ አመቻችና ተዘዋዋሪ መምህራን ተሳትፈዋል::
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/aacaebc