Addis Ababa Education Bureau
Addis Ababa Education Bureau
March 1, 2025 at 04:56 PM
አፍሪካዊ የትምህርት ምዘና ስርዓት እንዲዘረጋ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ፡፡ (የካቲት 22/2017 ዓ.ም) የትምህርት ምዘና እና የፈተና አሰጣጥ ስርዓት አህጉራዊ ይዘት ባለው ማዕቀፍ እንዲመራ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማህበር ገለጸ። ማህበሩ በመጪው ነሐሴ 2017 ዓ/ም ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄደው አህጉር አቀፍ የትምህርት ምዘና ጉባኤ የዝግጅት ስራዎችን ገምግሟል። የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማህበር ፕሬዚዳንት ማፉ ኤስ ራኮሜቲስ ፥ ማህበሩ አፍሪካ የራሷ የሆነ የትምህርት ምዘና ስርዓት እንዲኖራት ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። ድሕረ-ቅኝ ግዛት በርካታ ሀገራት ስርዓተ-ትምህርታቸውን በራሳቸው ማዕቀፍ ቢመሩም አሁንም ግን ከቅኝ ገዢዎች ስርዓት ትምህርት ያልተላቀቁ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ማህበሩ አፍሪካዊ ስርዓተ-ትምህርት እና የምዘና ስርዓት ይዘት ዕውን እንዲሆን የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጠዋል። የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንትና የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፥ የትምህርት ምዘና ስርዓቱን በአህጉር ደረጃ የተጣጣመ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም ፥ በአፍሪካ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ስርዓት ሊሚያሟሉ በሚገባቸው ደረጃ ላይም በጉባኤው በስፋት ውይይት እንደሚያደርግም ገልፀዋል። 33 የአፍሪካ ሀገራት የተካተቱበት ማህበሩ በቀጣይ በሚካሔደው አህጉር አቀፍ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የማህበሩን ፕሬዚዳንትነት እንደምትረከብም መገለጹን የዘገበው ኢዜአ ነው። ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች https://linktr.ee/aacaebc

Comments