ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
February 24, 2025 at 09:28 AM
የካቲት 17 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች #ሔዝቦላህ የሊባኖሱ የጦር ድርጅት(ሔዝቦላህ) የቀድሞ መሪ የሐሰን ናስረላህ የቀብር ስነ ሥርዓት ትናንት ተፈፀመ፡፡ ናስረላህ ከመንፈቅ በፊት እስራኤል በሊባኖሷ ርዕሰ ከተማ ቤይሩት በፈፀመችው የአየር ድብደባ መገደላቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በተኩስ አቁም እስከተገታ ድረስ እስራኤል በሊባኖስ የተለያዩ ክፍሎች ጥቃት ስታደርስ ቆይታለች፡፡ ከናሰረላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈፀም በፊት በቤይሩት ትልቅ ስታዲዮም የሐዘን መታሰቢያ ተደርጎላቸዋል፡፡ በሥነ - ሥርዓቱም የሔዝቦላህ አባላትን ጨምሮ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ የናስረላህ ምክትል የነበሩት የሐሺም ሳፈዲንም የቀብር ሥነ-ሥርዓትም አብሮ መፈፀሙ ታውቋል፡፡ #ጀርመን በጀርመን በተካሄደው ምርጫ የወግ አጥባቂዎች (CDU/CSU) የፖለቲካ ማህበር በመሪነት አጠናቀቀ፡፡ የወግ አጥባቂዎቹ የፖለቲካ ማህበር በምርጫው በመሪነት ያጠናቀቀው ከተሰጠው ድምፅ የ28 ነጥብ 6 በመቶ ውጤት በማግኘት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡ አማራጭ ለጀርመን የሚሰኘው AFD የፖለቲካ ማህበር ደግሞ ሁለተኛ ሆኗል፡፡ SPD የተሰኘው ግራ ዘመም የፖለቲካ ማህበር 3ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ በጀርመን ከጥቂት ወራት በኋላ በዚሁ የምርጫ ውጤት መሰረት አዲስ ጥምር መንግስት እንደሚቋቋም ታውቋል፡፡ የወግ አጥባቂዎቹ የፖለቲካ ማህበር የበላይ ፍሬድሪክ ሜርዝ የጀርመን ቀጣዩ መራሄ መንግስት ይሆናሉ ተብሏል፡፡ #የመን የየመን ሁቲዎች በአሜሪካ F 16 የጦር ጄት ላይ ከምድር ወደ አየር ተምዘግዛጊ ሚሳየል ተኮሱ ተባለ፡፡ ሁቲዎቹ በአሜሪካው የጦር አውሮፕላን ላይ ሚሳየል የተኮሱት ከ5 ቀናት በፊት እንደሆነ የፔንታገን ሹሞች መናገራቸውን ፎክስ ኒውስ መዘገቡን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡ በአሜሪካው የጦር አውሮፕላን ላይ በሁቲዎቹ ሚሳየል የተተኮሰበት በየመን የባህር ዳርቻ አቅራቢያ የአየር ክልል መሆኑ ታውቋል፡፡ ሆኖም አውሮፕላኑ በተተኮሰበት ሚሳየል አልተመታም ተብሏል፡፡ ተጨማሪ ያንብቡ... https://tinyurl.com/ay9s8ups

Comments