
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
8.1K subscribers
About ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
ሸገር 102.1 መስከረም 23፣2000 ዓ.ም ሥራ የጀመረ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ ጣቢያችን ለማንም ባለመወገን ለሁሉም በታማኝነትና በመልካም ሥነ ምግባር መልካም አገልግሎት በመስጠት የሚያምንና ለእነዚህም እሴቶች ትልቅ ክብር የሚሰጥ ሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ ሸገር የእናንተ ነው! https://bit.ly/33KMCqz
Similar Channels
Swipe to see more
Posts

ሰኔ 5 2017 በሰላም እጦት ምክንያት ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ገራዶ አካባቢ ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች በድንገት መኖሪያችን እየፈረሰ ነው እኛም ለዳግም መፈናቀል ልንዳረግ ነው ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ እስካሁን ልቀቁ እንዳልተባሉና መፍትሄ ሳያገኝ እንደማያስነሳቸው ተናግሯል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ አካባቢ በነበረ የሰላም እጦት ምክንያት ቀያቸውን ለቀው የወጡ ከ700 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ከሶስት አመት በላይ በደቡብ ወሎ ዞን ገራዶ ተብሎ በሚጠራ ቦታ መጠለያ ተሰጥቷቸው እየኖሩ እንደነበር ነግረውናል፡፡ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ተጠልለው የሚኖሩበት መጠለያ ለባለሀብት ተሽጧል በሚል ምክንያት ካለምንም ምትክ ቦታ ሜዳ ላይ እየወጣ ነው የሚሉት ተፈናቃዎቹ እስካሁን ሶስት አባዎራዎች ተጠልለውበት የነበረ የሸራ ቤት ፈርሷል ይላሉ፡፡ ከዚህ በፊት ቦታው ለባለሃብት ተሽጧል ትነሳላችሁ የሚል ጭምጭምታ ብንሰማም ማንም ሰው ወደኛ መጥቶ ህጋዊ በሆነ መንገድ አልነገረንም ነበር ሲሉ ተፈናቃዮቹ ያስረዳሉ፡፡ አሁን ግን በድንገትና ባልጠበቅነው ሁኔታ ህፃናት፣ ነፍሰጡር እናቶች ፣ አካል ጉዳተኞችና አዛውንቶቹን ይዘን ሜዳ ላይ ልንቀረው ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ነግረውናል፡፡ ለደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት ስለ ጉዳዩ ብናሳውቅም መፍትሄ መስጠት የምንችለው የምግብ ችግር ቢሆን ነው ሲሉ መልሰውልናል፡፡ እኛም በደሴ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ቃሲም አበራን ጠይቀናቸዋል፡፡ እሳቸውም መሬቱ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ለአንድ ባለሀብት እንደተሰጠ በፍቃዱ ተፈናቃዮች እንዲኖሩበት እንደሰጣቸውና አሁን ወደ ስራ መግባት ስለፈለገ እንዲለቁ መጠየቁ ነግረውናል፡፡ ለተፈናቃዮች ተቀያሪ መጠሪያ ሳይመቻችላቸው እንደማይነሱም አቶ ቃሲም ለሸገር ተናግረዋል፡፡ ማርታ በቀለ https://tinyurl.com/3ssraaa8

ሰኔ 5 2017 ዛሬ በምክር ቤት ሹመታቸው የፀደቀላቸው የምርጫ ቦርድ የስራ ሀላፊዎች ቀጣዩን ምርጫ ፍትሃዊ ና ታዓማኒ ለማድረግ እንዲሰሩ ተጠየቁ፡፡ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ በካሄደው መደበኛ ጉባኤው ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት ሆነው ሲገለግሉ የቆዩትን አቶ ተስፋዬ ንዋይን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሆኑ የቀረበለትን ውሳኔ አጽድቋል፡፡ ምክር ቤቱ በዛሬው ስበሰባው በትግራይ ክልል በተለያዩ ሃላፊነት ላይ የሰሩትን፤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት ሆነው ሲገለግሉ የቆዩትን አቶ ተክሊት ይመስል እና በሃረሪ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከፍተኛ ዳኛ ሆነው ሲገለግሉ የቆዩትን ወ/ሮ ነሲም አሊ የቦርድ አባል እንዲሆኑ የቀረበለትን ውሳኔ አጽድቋል፡፡ ሹመታቸውን በተመለከተ ሃሳባቸውን የሰጡት የምክር ቤት አባሉ ዶ/ር አበባው ደስአለው ነፃ እና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ የምርጫ ቦርድ ዋነኛ ስራው ቢሆንም እስካሁን ባለው ሁኔታ ነፃ እና ገለልተኛ ምርጫ አለመካሄዱን የተለያዩ አካላት በቅሬታ እንደሚቀርቡ ተናግረው ተሿሚዎቹ ተቀጣዩን ምርጫ ነፃ እና ተአማኒ ለማድረግ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው አዲስ ተሿሚዎቹ በትምህርት ዝግጅትም ሆነ በስራ ልምድ ብቁ መሆናቸውን ተናግረው ቀጣዩን ምርጫ ግልጽ እና ፍትአዊ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ቤልጅጌ ተሿሚዎችን በተመለከተ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት መካሄዱን ተናግረው በህገ-መንግስቱ እና በምርጫ ህጉ መሰረት አዲሶቹ ሃላፊዎች የሚካሄዱ ምርጫዎችን እና ህዝብ ውሳኔዎችን ገለልተኛ ሆኖ ለማካሄድ ይሰራሉ ብለዋል፡፡ ያሬድ እንዳሻው ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ. https://tinyurl.com/2vdjxxpc

ታሪክን የኋሊት ሰኔ 5 2017 በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፖብሊክ ፣ ራሱን አንግሶ፣ አጼ በጉልበቱ የነበረው ጄን ቤዴል ቦካሳ የይሙት በቃ ፍርድ የተፈረደበት በ1979 ዓ.ም በዛሬዋ እለት ነበር፡፡ ቦካሳ በቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ በወታደርነት ፣ በኢንዶ ቻይናና በአፍሪካ አገልግሏል፡፡ አገሩ ነፃ ከወጣች በኋላ በመከላከያ በሻለቃ አዛዥነት ተመድቦ ፣ በማዕረግም ወደ ኮሎኔልነት አደገ፡፡ ወደ ስልጣን እርከኑ የመጨረሻ ከፍታም፣ ጠጋ ጠጋ ያለው የሃገሪቱ የጦር ሀይሎች ኢታማዦር ከሆነ በኋላ ነበር፡፡ የጦር አዛዥነቱን ተጠቅሞ፣ ከግብረ አበሮቹ ጋር የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበረው ዴቪድ ዳከን በመፈንቅለ መንግስት አስወገደው፡፡ ዴሞክራሲ ሲመጣ፣ ፍትህ ሲነግስ፣ እና እኩልነት ሲደላደል፣ ስልጣኑን አስረክባለሁ ብሎ የመሪነቱን ስልጣን ጨበጠ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ወደ ለየለት አምባገነንነት ጭልጥ ብሎ ገባ፡፡ ሕዝቡን በብረት መዳፍ ቀጥቅጦ እና አንቀጥቅጦ ገዛው፡፡ ሃገሪቱን እንደ ግል ንብረቱ ቆጥሮ የፈለገውን አደረገባት፡፡ ቃሉን ሕግ አድርጎ ሕዝቡን እያስረ፣ እየጨቆነ እየገደለ መከራውን አሳየው፡፡ ቦካሳ ፕሬዘዳንት መሆኑ ብቻ አላረካውም ፡፡ ስለዚህ የእድሜ ልክ ፕሬዘዳንት ነኝ ብሎ አወጀ፡፡ ይሄም አልበቃውም፡፡ ራሱን አፄ አሰኝቶ ዘውድ ጭኖ ንጉስ ሆኛለሁ አለ፡፡ በዓለ ሲመቱን ለማክበር ለ2 ቀናት ዝግጅት፣ ከ20 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ አደረገ፡፡ ይሄ ከዚያን ጊዜ የማዕከላዊ አፍሪካ የአመት በጀት ፣ ከሲሶ በላይ ነበር፡፡ ሕዝቡ ግን በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ማብቂያ አለውና፣ የቦካሳን አምባገነናዊ አገዛዝ ለማስወገድ በጉብኝት ሊቢያ ሳለ መፈንቅለ መንግስት ተካሄደ፡፡ ወታደሮች አሴሩ፡፡ መፈንቅለ መንግስቱን፣ ፈረንሳይም ትደግፈው ስለነበር ፣ ከትሪፖሊ ፣ ፓሪስ ሲደርስ ግዞተኛ አደረጉት፡፡ የስደት ጊዜውን በኮትዲቭዋር እንዲያደርግ ጠይቆ ስለተፈቀደለት ወደዚያው ሄደ፡፡ እጁ ተይዞ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ሞት ተፈረደበት ፡፡ ከሰባት አመታት እስራት በኋላ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ተመለሰ፡፡ ከጥቂት አመታት እስር በኋላ ለእስረኞች ይቅርታ ሲደረግ ይቅርታ ተደርገለት፡፡ ከሶስት ዓመታት በኋላ በህመም ምክንያት አረፈ፡፡ ጄን ቤዴል ቦካሳ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት 38 ዓመት ሆነ፡፡ እሸቴ አሰፋ https://youtu.be/7cgOGhmy5FY

ሰኔ 5 2017 የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት ያጣነው ሃይማኖትን ከፖለቲካ ፖለቲካን ከሃይማኖት ስለምንቀላቅል ነው፡- አቡነ አብርሃም በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ከመጣፋፋት ይልቅ ወደ ሰላም እንዲመጡ የሃይማኖት አባቶች ተማፅነዋል፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የእርስ በእርስ ጦርነቶችና ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ጥሪያቸውን የሚያቀርቡት የሃይማኖት አባቶቹ ዛሬም ድረስ የቀጠለው ግጭት እዲያበቃ እየተማፀኑ ነው፡፡ በባህር ዳር ከተማ በተሰናዳው ሶስተኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ኮንፈረንስ የሃይማኖት አባቶቹ ይህንኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው መርሃ ግብር ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም "ለገጠመን የሰላም እጦት መነሻው ጠባጫሪ ንግግር ነው ፣ከዚህ እንቆጠብ ያሉት ሊቀ ጳጳሱ ምንም እንኳን መሰል የሰላም ጥሪዎችን ስናስተላልፍ ብንከርምም ተሰሚነት አጥተናል "ብለዋል፡፡ "ይህም የሆነው እኛ የሃማኖት አባቶች ሃይማኖትን ከፖለቲካ ፖለቲካን ከሃይማኖት እየቀላቀልን ህዝቡን ግራ በማጋባታችን ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡ "በግጭት ውስጥ በግራና ቀኝ የተሰለፋችሁ ልጆቻችን የሰላም ጥሪያችንን ተቀብላችሁ ወደ መነጋገር እንድትመጡ" ሲሉም ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተማጽነዋል፡፡ በተጨማሪም በመድረኩ ተገኝተው የሰላም ጥሪያቸውን ያስተላለፉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንትና የሃማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለዘመናት ሲፈትናት የቆየው የደህንነት ማጣትና ድህነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አፈሙዝን እያስቀደሙ ወደ ስልጣን የሚመጡ ፖለቲከኞች የደህንነታችን ስጋት ሆነው ቆይተዋል፤በዚህም ምክንያት አንዱ የሰራውን ሌላው ስለሚያፈርስ በድህነታችን ቀጥሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ "ፈተናችን እንዲያበቃ ወደ መነጋገር መሸጋገር አለብን እዚህ ላይ እንበርታ" ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አቢያተ ክርስቲናት ካውንስል ጠቅላ ፀሃፊ ቄስ ደረጀ ጀምሩ ጦርነት እንደ ሃገር አድቅቆናል ከዚህ በላይ የሚያስከትለውን ጉዳት የመሸከም አቅም አይኖረንምና ጦርነት፣ግጭት፣አለመግባባት በቃን እንበል፤ሰላም ህዝቡ ሰላንም ተርቧል፤እያሳለፈው ካለው ሰቆቃ እናሳርፈው ሲሉ እርሳቸውም በሁሉም ወገን ያሉ ተፋላሚዎችን ወደ ሰላም ኑ ሲሉ ተማፅነዋል፡፡ ምንታምር ፀጋው ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ. https://tinyurl.com/3j5cw5wj

ሰኔ 5 2017 በግብይት ወቅት ከ 10 ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብን መጠቀም፣ለከፋዩ በወጪነት፣ለተቀባዩ ደግሞ አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጣልበት ያደርጋል ተባለ። አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ሲጸድቅ ከ10,000 ብር በላይ ግብይትን በጥሬ ገንዘብ መፈጸም የሚያስቀጣ ይሆናል ተብሏል። ረቂቅ አዋጁ ላይ ሃሳብ ለማዋጣት ከተሳተፉ ባለሙያዎች የተወሰኑት ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው አሰራር ላይ ጥያቄ አንስተዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር የህግ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊው አቶ ተወዳጅ መሐመድ እንዳሉት አዋጁ ተግባራዊ የሚደረገው በጥሬ ገንዘብ የሚፈፀም ግብይትን መገደብን ታሳቢ አድርጎ ነው። በአንድ ግብይት የሚፈፀም የጥሬ ገንዘብ ክፍያ ከ10ሺህ ብር ከበለጠ፣ትርፉ ብር ለከፋዩ በወጪነት አይያዝም።ገንዘቡን የተቀበለውም የትርፉን ገንዘብ እጥፍ አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበት ተቀምጧል።ለምሳሌ የ20ሺህ ብር ግብይት በጥሬ ገንዘብ ቢፈፀም ለነጋዴው፣ከ10 ሺህ ብር በላይ ያለው በወጪነት አይያዝም፣ለተቀባዩ ደግሞ ከ10ሺህ በላይ ያለው ቀሪ 10ሺህ ብር እጥፍ ማለትም 20ሺህ ብር ይቀጣል እንደማለት ነው። በረቂቅ አዋጁ ላይ የተሳተፉ፣በጥሬ ገንዘብ ግብይት እንዲፈፀም ምክንያት የሚሆነውን በንግድ ስርዓቱ ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችልና፣በሌሎች መመሪያዎች የጥሬ ገንዘብ ግብይት ስለሚፈቀድ አዋጁ የተናበበ እንዲሆን ጠይቀዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ባሰናዳው ረቂቅ አዋጅ መሰረት ከ10ሺህ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ግብይት እንዳይፈፀም የሚጣለው ግዴታ፣በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣በመንግስት የልማት ድርጅቶች፣በባንኮችና በማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም ይላል። ሌሎች አዋጁ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ ዝርዝራቸው ይፋ ይሆናል ይላል ረቂቁ። ቴዎድሮስ ወርቁ ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ https://n9.cl/yj5t7r

ሰኔ 6 2017 የገቢ ግብር አዋጅ ተሻሽሎ ረቂቅ ተሰናድቶለታል፡፡ ደመወዝተኛውን በተመለከተ ምን ያህል ደመወዝ ላይ፤ መንግስት ምን ያህል በመቶ ግብር ይቁረጥ የሚለው በረቂቁ ላይ አልሰፈረም፡፡ ለውይይትም ክፍት ሆኗል፡፡ ይሁንና ገንዘብ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባሰናዳው የውይይት መድረክ ላይ ግብር የማይቆረጥበት ዝቅተኛው የደመወዝ መጠን ከ2,000 ብር ጀምሮ ይሆናል የሚል አቋም እንዳለው ተናግሯል፡፡ ከ10,900 ብር ጀምሮም በነበረው 35 በመቶ ግብር እየከፈሉ እንደሚቀጥሉ መንግስት አቋሙን አሳውቋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ያለውንና በመጭው ጊዜይም እየባሰ ይመጣል ያሉትን የመግዛት አቅም መዳከም አንስተው ማሻሻያው እንደገና ይታይ እያሉ ነው፡፡ ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ… https://tinyurl.com/y2jabs49 ትዕግስት ዘሪሁን የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… 📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1 📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX 📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s 📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il

ሰኔ 6 2017 የእስራኤል ጦር በኢራን ላይ ከባድ ድብደባ ፈፅሜያለሁ አለ፡፡ ጦሩ ድብደባዬ በኢራን የኒኩሊየር ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ነው ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡ አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል አዛዥን ሁሴን ሰላምን ገድያለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ሌሎች የኢራን የጦር አዛዦችም በድብደባው መገደላቸው ታውቋል፡፡ የኢራን መንግስታዊ ቴሌቪዥን፤ እስራኤል በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ በፈፀመችው ድብደባ ሕፃናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎችን ገድላብናለች ሲል ዘግቧል፡፡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ኢራን ለእስራኤል ሕልውና እጅግ አደገኛ ሀገር ነች ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ እስራኤል የአፀፋው ጥቃት ሊሰነዘርባት እንደሚችል ገምታለች፡፡ በዚህም የተነሳ የአስቸኳይ ጊዜ ስራ ላይ ማዋሏ ታውቋል፡፡ የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… 📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1 📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX 📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s 📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


ሰኔ 5 2017 ወደ እንግሊዝ ለንደን ለማምራት የተነሳ የህንድ የመንገዶች አውሮፕላን ተከሰከሰ፡፡ 242 ሰዎችን ያሳፈረው አውሮፕላን የተከሰከሰው ከአህመድአባድ ኤርፖርት እንደተነሳ ወዲያውኑ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡ አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ስፍራ ከባድ ጭስ እየተትጎለጎለ ነው ተብሏል፡፡ የወደቀው አውሮፕላን ቦይንግ 787 ድሪም ላይነር መሆኑ ታውቋል፡፡ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ቃጠሎው ለማጥፋት እየታገሉ ነው ተብሏል፡፡ ከአደጋው በሕይወት የተረፉ ሰዎች ስለመኖራቸው የተሰማ ነገር የለም፡፡ አደጋ የገጠመው አውሮፕላን የኤር ኢንዲያ አየር መንገድ ንብረት መሆኑ ታውቋል፡፡ የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… 📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1 📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX 📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s 📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


አንጋፋዋ ተወዳጇ ጋዜጠኛ ብርቱኳን ሐረገወይን በየያኔዎቹ ! https://youtu.be/7pwNj2XATWc