
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
February 25, 2025 at 02:31 PM
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ዩ ሪፖርት (U- Report) ለወጣቶች የሚተላለፉ አጭር የፁሁፍ መልዕክቶችን በነፃ ለመላክ ተስማማ።
በዩኒሴፍ ዓለምአቀፍ የተዘጋጀው ዩ ሪፖርት የወጣቶች መልዕክት መለዋወጫ ስርዓት ወጣቶች ለአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጠትና ድጋፍ ማድረግ የመሳሰሉ የማህበራዊ እድገትን የሚያመጡ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ እንዲችሉ ግንዛቤ ለመስጠት የተዘጋጀ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በ99 አገሮች ከ36.1 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ስርዓቱ በወጣቶች ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ ሲሆን በኢትዮጵያም ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ የተመሰረተ ሲሆን እስካሁን ከ17ሺ በላይ አባላት አሉት ተብሏል።
ስምምነቱ የስርዓቱ አባል የሆኑ ወጣቶች ለአንድ ዓመት ያለክፍያ መልዕክት እንዲደርሳቸው የሚያስችል ነው።
ይህ ጥምረት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወጣቶችን ለማገዝ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል የተባለ ሲሆን በተለይ በገጠሩ አከባቢ ያሉ ወጣቶች ጠቃሚ መረጃዎችን እንዲያገኙና በዙሪያቸው ካሉ ጋር በበለጠ እንዲግባቡ ያስችላቸዋል ተብሎለታል።
በትምህርት፣ በጤና እና ማህበራዊ እድገት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን ለማሰራጨት እድል የሚሰጥ ሲሆን ቅንጡ የስልክ ቀፎ የሌላቸውን ታሳቢ ያደረገ ነው ሲባል ሰምተናል።
ስመምነቱን የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ፈርመውታል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደንበኞቼ 8 ሚሊዮን ደርሰዋል ያለ ሲሆን ከአገሪቱ ህዝብ ግማሹን መድረስ የሚያስችል ኔትወርክ ዘርግቻለሁ ብሏል።