ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
February 28, 2025 at 04:40 PM
የካቲት 21 2017 በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት በግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚከውኑ ፕሮጀክቶች ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ባሉ 5 ወረዳዎች በ56 ቀበሌዎች በጀርመን መንግስት በተገኘ የ8.8 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ 163 የውሃ ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል፡፡ ጀርመን አግሮ አክሽን ከሌሎችም አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ከ2008 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም አጋማሽ በከወነው በዚህ የውሃ ፕሮጀክት 163 የውሃ ፕሮጀክቶችን በመስራት የአካባቢውን የውሃ አቅርቦት ወደ 45 በመቶ ማድረሱን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ወርቁ ነግረውናል፡፡ በፕሮጀክቱ ትግበራ ወቅት በተለይ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የብር የመግዛት አቅም በመዳከሙ የመጣው የዋጋ ንረት የፀጥታ ችግሮችና ውሃ የማይገኝባቸው የመከኑ ግድጓዶች መኖር እንቅፋት እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል የውሃ ኢነርጂ ቢሮ በበኩል ለፕሮጀክቱ ትግበራ በየአዓመቱ ከ6 እስከ 10 ሚሊዮን ብር በመመደብ ሲያግዝ መቆየቱን የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው ነግረውናል፡፡ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱ ከ54 በመቶ ያልበለጠ እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ይህ ፕሮጀክት የተተገበረባቸው የምስራቅ ጎጃም ወረዳዎች ከፍተኛ የሃይል አቅርቦት ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ የክልል የውሃ ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊው ዶክተር ማማሩ አያሌው በአካባቢው የኤሌክትሪክ ሃይል ባለመኖሩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ስራው የተሰራው የሶላር ኤነርጂን በመጠቀም እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል የአሜሪካ መንግስት የተራድኦ ድርጅት የሆነው ዩ ኤስ አይ ዲ የሚሰጠውን ድጋፍ ማቋረጡ በውሃ አቅርቦት ስራዎች ላይ ምን ተፅዕኖ አሳደረ? ልናቸው ሃላፊው እስካሁን ምንም አይነት ተፅዕኖ አላሳደረም ብለዋል፡፡ ለ8 ዓመታት በተተገበረው የጆን ሪሽ ዋሽ ፕሮግራም በውሃ አቅርቦትና የአካባቢውን ንፅህና በማስጠበቅ በ56ቱም ምስራቅ ጎጃም ዞን ቀበሌዎች 280 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን መድረስ እንደተቻለ ሰምተናል፡፡ ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ… https://tinyurl.com/2sbs2vz9 ምንታምር ፀጋው የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… 📌 Website: https://shorturl.at/yCz7q 📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd 📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s 📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il 📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r

Comments