
Ethiopian Embassy In Djibouti - የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጅቡቲ
February 11, 2025 at 06:44 AM
*ኤምባሲው የምግብ ዘይት ኦፕሬሽን ኮሚቴን አወያየ፤*
ኤምባሲው ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ግዥ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ያለውን የምግብ ዘይት የኦፕሬሽን ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካላቸው ተቋማት ጋር በኤምባሲው አወያይቷል።
በውይይቱም የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወር የምግብ ዘይት ዝውውር አፈጻጸም እና በቀጣይ መሻሻል ያሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
የዘይት ማጓጓዝ ስራን ማቀላጠፍ፣ የአገልግሎት ጥራት እና ቁጥጥር ክፍተቶች ለማሻሻል፣ የመረጃ ልውውጥ ሂደትን ማጠናከር፣ ምርቱን በወቅቱ ማድረስ እና ሌሎች ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል።
ኤምባሲውም የዘንድሮው የዘይት ኦፕሬሽን አፈጻጸም ከባለፈውም ዓመት የተሻለ መሆኑን በማንሳት፣ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ሁሉም የሚመለከተው አካል በፍጥነት እንዲያስተካክል አሳስቧል።
በተለይም ከፊታችን ያሉ የበዓል ጊዜያትን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ እና በመድረኩ ለተነሱ ጉዳዮች ኤምባሲው በቀጣይ በጂቡቲ እና በአገር ውስጥ ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ማቀዱን ገልጿል።
ተሳታፊዎችም የሎጂስቲክ አገልግሎት ቅልጥፍናን ለመጨመር የተነሱ ክፍተቶችን በማረም እና በቀጣይ ተፈጻሚነታቸውን ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የዘይት አቅራቢ ድርጅት ኃላፊዎች፣ በጂቡቲ የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጅስቲክስ ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጽ/ቤት ተወካዮች ተሳትፈዋል።