Ethiopian Embassy In Djibouti - የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጅቡቲ
Ethiopian Embassy In Djibouti - የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጅቡቲ
February 28, 2025 at 10:50 AM
ክቡር ሚኒስትሩ በጅቡቲ እየተከናወነ ባለው የሎጂስቲክስ ውጤታማ ስራ አድናቆታቸውን ገለጹ፤ (የካቲት 21/2017 ዓ.ም) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ ዛሬ በጂቡቲ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ተገኝተው በጅቡቲ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር ከጂቡቲ-ኢትዮጵያ ባለው አጠቃላይ የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ ላይ ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸውም የአፈር ማዳበሪያ ዝውውርን አስመልክቶ በተለይም በኤምባሲው የሚመራው የአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴ እያስመዘገበ ያለውን ከፍተኛ አፈጻጸም እውቅና በመስጠት ለኮሚቴው አባላት እና በዘርፉ ላሉ የተቋማት ኃላፊዎች ልዩ ምስጋና አቅርበዋል። አክለውም የማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴው በቅንጅት በመስራቱ በአንድ ቀን ከ18 ሺ ሜ/ቶ በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ማስገባት መቻሉ በእጅጉ ሊበረታታ እንደሚገባ ገልጸዋል። ከማዳበሪያ ኦፕሬሽኑ በተጨማሪ በሌሎች የሎጂስቲክስ ስራዎች ላይ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አጠቃላይ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ተቋማትን በማቀናጀት በተሰራው ስራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ የቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል። ክቡር ሚኒስትሩ የኢትዮ-ጂቡቲ ኮሪደር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ከመፍታት አንጻር በአፈር ማዳበሪያ ግዥ፣ ከጅቡቲ ወደ አገራችን የሚጫኑ ካርጎዎች፣ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ላይ የሚከሰቱ ከጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ሰጥተዋል። በዚህ መሠረት የትራንስፖርት ዝውውሩን ለማሳለጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ስራ ኢትዮጵያ ባለው አብይ ኮሚቴ በኩል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አሳውቀዋል። ክቡር ሚኒስትሩ የአፈር ማዳበሪያ የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት በተቻለ ፍጥነት ተጓጉዞ ለአገራችን አርሶ አደሮች እንዲደርስ ኦፕሬሽን ኮሚቴው እያከናወነ ያለውን ውጤታማ ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል። በመጨረሻም ከከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የሎጂስቲክስ ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች እና ሚሲዮኑ በጂቡቲ ያለው ከባድ የአየር ሁኔታ ሳይበግራቸው ሌትተቀን በወደቦች በመገኘት ሀገር የሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት እያበረከቱ ላለው አስተዋጽዖ አመስግነዋል።

Comments