DW Amharic

DW Amharic

185.2K subscribers

Verified Channel
DW Amharic
DW Amharic
June 7, 2025 at 04:44 PM
የግንቦት 30 ቀን 2017 የዓለም ዜና • የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች እና አክቲቪስቶች “ጦርነት ይቁም፣ ግፋዊ አገዛዝ ይብቃ፣ ሰላም ይምጣ” የሚል ጥሪ ያቀረቡበትን ትዕይንተ-ሕዝብ በበይነ-መረብ አማካኝነት እያካሔዱ ነው። በመርሐ-ግብሩ ከተሳተፉ መካከል ራሔል ባፌ፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ጀዋር መሐመድ እና ዘመነ ካሴ ይገኙበታል። ትዕይንተ-ሕዝቡን ያቀናጀው የአብሮነት ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ልደቱ አያሌው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ አራት ፖለቲከኞች ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘው ሳይገኙ መቅረታቸውን ተናግረዋል። • በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች “በፖለቲካዊ እና የብሔር ልዩነት ምክንያት የተቀሰቀሰ የትጥቅ ግጭት እየተባባሰ” መሔዱን በአውሮፓ ኮሚሽን ሥር የሚገኘው የአውሮፓ የሲቪል ጥበቃ እና የሰብአዊ ርዳታ ሥራ ክፍል አስታወቀ። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ ከ11,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጿል። • በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በተከሰተ ጎርፍ 1753 አባወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የአካባቢው መንግሥት አስታወቀ። በወረዳው በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት በአጠቃላይ 8445 ሰዎች “ዳግም” መፈናቀላቸው ተገልጿል። • የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኙ ነዋሪዎች መንደራቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጠ። እስራኤል ዛሬ ቅዳሜ በጋዛ ሠርጥ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች 45 ሰዎች መገደላቸውን የሕክምና የመረጃ ምንጮች እንደተናገሩ ሬውተርስ ዘግቧል። • በምሥራቃዊ ዩክሬን በምትገኘው ኻርካይቭ ከተማ ላይ ሩሲያ በድሮኖች እና ሚሳይሎች በፈጸመችው ከፍተኛ ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ 21 መቁሰላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ። ሁለቱ ሀገሮች በጦር ምርኮኞች እና የሟች ወታደሮች አስከሬን ልውውጥን በተመለከተ እየተወዛገቡ ነው። የዕለቱን ዜና ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ፦ https://shorturl.at/bxFja
👍 🧘‍♂️ 🫵 3

Comments