
DW Amharic
June 12, 2025 at 11:24 AM
ፖርት ሱዳን-የሱዳን ጦር ኃይል ሐፍጣርን ወነጀለ
የሱዳን መከላከያ ጦር የሊቢያ የጦር አበጋዝ ኸሊፋ ሐፍጣር የሚያዙት ሚሊሺያ ጦር ጥቃት እንደከፈተበት አስታወቀ።የሱዳን መከለከያ ጦር አዛዦች እንደሚሉት ሱዳንን ከሊቢያና ከግብፅ ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር ላይ የሠፈረዉ ጦራቸዉ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርና በኸሊፋ ሐፍጣር ኃይላት የተቀናጀ ጥቃት ተከፍቶበታል።ሶስት ማዕዘናማዉ አካባቢ ሠፍሮ የነበረዉ የሱዳን መከላከያ ጦር ዳግም ለመደራጀት ከአካባቢዉ ማፈግፈጉን አዛዦቹ አስታዉቀዋል።የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ለረጅም ጊዜ ከከበባት ከአል ፋሻር ከተማ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘዉ ድንበር ሠፍሮ የነበረዉ ጦር በአብዛኛዉ ከቀድሞ አማፂ ኃይላት ተዋጊዎች የተዉጣጣ ነዉ።የሐፍጣርና የፈጥኖ ደራሹ ኃይላት የድንበሩን መተላለፊያ፣ ጦር መሳሪያ ለማሻገር ይጠቀሙበታል በማለትም የሱዳን መከላከያ ጦር ይወቅሳል።የሐፍጣር ኃይል ግን ወቀሳዉን አስተባብሏል።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ራሳቸዉን ፊልድ ማርሻል ብለዉ ለሚጠሩት ኸሊፋ ሐፍጣር ከፍተኛ ድጋፍ ከሚሰጡ መንግሥታት አንዷ ናት።የሱዳን መከላከያ ጦር ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦርን ትረዳለች በማለት በተደጋጋሚ ይወቅሳል።
