DW Amharic

DW Amharic

185.2K subscribers

Verified Channel
DW Amharic
DW Amharic
June 12, 2025 at 02:06 PM
መቀሌ-የትግራይ የርስበርስ ግጭት ሥጋትና የሲቪክ ማሕበራት ጥሪ በትግራይ ክልል ያንዣበበዉ የእርስበርስ ግጭት ስጋት እንዲቀረፍ የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር መጣር እንዳለበት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁለት ሲቪክ ተቋማት ጠየቁ። ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች እና የዴሞክራሲና የማሕበራዊ ፍትህ ድምፅ የተባሉት ሲቪክ ተቋማት ባወጡት መግለጫ እንደሚሉት በትግራይ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት በክልሉ የእርስበርስ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ሥጋት አስከትሏል።ሥጋቱ አሳሳቢ እና የትግራይ ህዝብ ሊቋቋመው የማይችል ነው ያሉት እነዚህ ሲቪክ ተቋማት ሥጋቱን ለማቃለል በትግራይ ያሉ ሁሉም አካላት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።የዴሞክራሲና ማሕበራዊ ፍትህ ድምፅ ስራ አስከያጅ አቶ መልአኩ ሃይሉ፥የትግራይ ሐይሎች ወታደራዊ መኮንኖች ባለፈው ጥር 15 ቀን 2017፣ አንድ የፖለቲካ ሃይልን ደግፈው መግለጫ ካወጡና የቀድሞዉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር 'በሐይል' ከስልጣን ከተወገደ በኃላ፣ በትግራይ ሐይሎች መካከል መከፋፈሎች መፈጠራቸው ያነሳሉ። ይህ ክፍፍል ሌላ ታጣቂ ሐይል እንዲፈጠር፥ የአደገኛ ግጭት ስጋት እንዲኖርም ማድረጉ ገልፀዋል። የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለሥላሴ እንደዘገበዉ የተወሰኑ የትግራይ ሐይሎች አባላትና አዛዦች በትግራይ አለ ያሉትን ስርዓት ለማስወገድ በአፋር እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ራሳቸውን ለነፍጥ ዉጊያ እያደራጁ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ በቅርቡ የተናገሩት የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ማንኛውም ፖለቲካዊ ልዩነት በሰላም መፍታት ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።
Image from DW Amharic: መቀሌ-የትግራይ የርስበርስ ግጭት ሥጋትና የሲቪክ ማሕበራት ጥሪ  በትግራይ ክልል ያንዣበበዉ የእርስበርስ ግጭት ...

Comments