DW Amharic

DW Amharic

185.2K subscribers

Verified Channel
DW Amharic
DW Amharic
June 15, 2025 at 01:52 PM
እስራኤል እና ኢራን አንዳቸው በሌላቸው ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ጨመረ። የእስራኤል ጦር የሀገሪቱ ዜጎች ከሕዝባዊ አደባባዮች በመራቅ ጥበቃ በሚደረግላቸው አካባቢዎች እንዲቆዩ አሳስቧል። ኢራን በበኩሏ መስጂዶች፣ የባቡር ጣቢያዎች እና ትምህርት ቤቶች ከዛሬ እሁድ ጀምሮ ከእስራኤል ጥቃት የሀገሬው ሕዝብ መሸሸጊያ እንደሚሆኑ አስታውቃለች። በሚሳይሎች እና ድሮኖች ጭምር የሚደረገው የእስራኤል እና የኢራን ውጊያ ሦስተኛ ቀኑን ሲይዝ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ብርቱ ጥቃት ለመፈጸም እየዛቱ ናቸው። የሁሉ ሀገሮች ውጊያ በካናዳ በሚካሔደው የቡድን ሰባት ሀገራት ጉባኤ ዋንኛ መነጋገሪያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። እስራኤል በተሒራን በሚገኘው የኢራን የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት እና ከሀገሪቱ የኑክሌር መርሐ-ግብር ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች። ኢራን በፊናዋ የእስራኤል የአየር መከላከያ ሥርዓት ጥሰው ባለፉ ሚሳይሎች የመኖሪያ ሕንጻዎችን ደብድባለች። በኢራን ጥቃት ለሊቱን ጨምሮ እስራኤል ውስጥ 10 ሰዎች መገደላቸውን ማገን ዴቪድ አዶም ተብሎ የሚጠራው የእስራኤል ብሔራዊ የድንገተኛ አደጋ የሕይወት አድን ብሔራዊ አገልግሎት አስታውቋል። በአጠቃላይ ባለፉት ሦስት ቀናት እስራኤል ውስጥ በኢራን ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 13 ደርሷል። የእስራኤል የአየር ክልል እና የሀገሪቱ ዋንኛ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ለሦስተኛ ቀን እንደተዘጉ ናቸው። እስራኤል በኢራን ላይ የምትፈጽማቸውን ድብደባዎች እንደቀጠለች ሲሆን ዛሬ እሁድ በማዕከላዊ ተሒራን ፍንዳታ እንደነበር የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። አርብ እና ቅዳሜ በተፈጸሙ የእስራኤል ጥቃቶች ብቻ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ 128 ሰዎች መገደላቸውን 900 ገደማ መቁሰላቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት የሀገሪቱን መገናኛ ብዙኃን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ በእስራኤል እና በኢራን ግጭት ጣልቃ ከገባች በቀጠናው የሚገኙ ይዞታዎቿ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር ቃጣኢብ ሒዝቦላሕ የተባለው የኢራቅ ታጣቂ ቡድን አስጠንቅቋል። ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ብሪታኒያ በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ በኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ላይ ከተሒራን ጋር በአፋጣኝ ለመነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሐን ቫደፑል ተናግረዋል። ብሪታኒያ በግጭቱ ምክንያት ዜጎቿ ወደ እስራኤል ከመጓዝ እንዲቆጠቡ መክራለች። እሸቴ በቀለ ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
Image from DW Amharic: እስራኤል እና ኢራን አንዳቸው በሌላቸው ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ጨመረ። የእስራኤል ጦር የ...
👍 ❤️ 😂 😢 😮 🤪 9

Comments