
Addis Ababa Education Bureau
June 3, 2025 at 10:05 AM
የአፍሪካ ቀዳማዊ ልጅነት ልማት ማዕከል በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባካሄደው ዳሰሳዊ ጥናት ግብረመልስ ዙሪያ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተካሄደ።
(ግንቦት 26/2017 ዓ.ም) ዳሰሳዊ ጥናቱ በ26 የመንግስት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ተግባራዊ የተደረገው ጫወታን መሰረት ያደረገው የማስተማር ስነ ዘዴ በህጻናቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ ምን እንደሚመስል እና ወደ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ለመሸጋገር ምን ያህል ዝግጁ እንደሆኑ ለማረጋገጥ መካሄዱን በውይይቱ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት የቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራም በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአግባቡ ተግባራዊ ሆኖ ህጻናቱ ጫወታን መሰረት ባደረገው የማስተማሪያ ስነዘዴ አማካይነት ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት መድቦ የግብአት አቅርቦትን እና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ጨምሮ በሚያደርጋቸው የተለያዩ ድጋፍና ክትትሎች ተቋማቱ ትራንስፎርም በመሆን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው የአፍሪካ ቀዳማዊ ልጅነት ልማት ማዕከል በዘርፉ የከናወኑ ተግባራት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ በጥናት በማረጋገጥ ምክረ ሀሳብ በማቅረቡ ምስጋና ለማዕከሉ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ቀዳማዊ ልጅነት ልማት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው ማዕከሉ ትኩረት አድርጎ ከሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች አንዱ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን መስራት እንደመሆኑ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ በመተግበር ላይ ያለው ጫወታን መሰረት ያደረገ የማስተማር ስነ ዘዴ በህጻናቱ ሁለንተናዊ ዕድገትም ሆነ ወደ 1ኛ ደረጃ ለመሸጋገር ምን ያህል ብቁ ናቸው የሚለውን ለማረጋገጥ ዳሰሳዊ ጥናት መደረጉን ገልጸው ማዕከሉ በጥናቱ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን መሰረት በማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአቅም ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቀረበው የዳሰሳዊ ጥናቱ ምክረ ሀሳቦችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን አቅርበው በትምህርት ቢሮ እና በማዕከሉ አመራሮች ምላሽ ተሰቷል።
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት ማሰፈንጠሪያውን ይጫኑ!
https://linktr.ee/aacaebc
