Addis Ababa Education Bureau
June 18, 2025 at 11:01 AM
በከተማ አስተዳደሩ የፊታችን ማክሰኞ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና መለማመጃ ፈተና ላይ የማይሳተፍ ተማሪዎች በዋናው ፈተና ላይ እንደማይቀመጡና ሁሉም ተማሪዎች እንዲገኙ ያላደረገ ትምህርት ቤት የሚጠየቅ መሆኑ ተገለጸ፡፡
(ሰኔ 11/2017 ዓ.ም) በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን በመርሀ ግብሩ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ባለሙያዎችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት አባላት ፤ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አመራሮች እንዲሁም የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ ለመጨረሻው የፈተና ልምምድ ምን መደረግ አለበት የሚልና በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ መሰረት ያደረግ ሰነድ በአቶ ዲናኦል ጫላ በትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ተካሄዳል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በይነ መረብ (online) ለሚሰጠው የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወናቸዉን በተጨማሪም መልቀቂያ ፈተናን በስኬት ለማጠናቀቅ ከትምህርት ሚኒስቴር ፣ ከኢትዮ ቴልኮምና ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት በተሰሩ ስራዎች በቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ የተሻለ ስራ ለመስራት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ገልጸዋል፡፡ ሀላፊው አክለዉም በቀጣይ ከዋናው ፈተና በፊት የፊታችን ማክሰኞ በሚደረገው የመጨረሻው መለማመጃ ላይ እንድም ተማሪ ሳይቀር መለማመጃዉን መውሰድ ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ መለማማጃ ላይ ያልተሳተፈ ተማሪ በዋናው ፈተና ላይ የማይሳተፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ተፈታኝ ተማሪዎች እንዲገኙ ያላደረገ ትምህርት ቤት የሚጠየቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀላፊው አክለዉም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሙሉ ለሙሉ በይነ መረብ (online) የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው ተፈታኝ ተማሪዎች አስፈላጊዉን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደረጉ የመለማመጃ ፈተናዎች ሲሰጡ መቆየታቸዉን ገልጸዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ዘንድሮ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በማህበራዊ ሳይንስ 23191 በተፈጥሮ ሳይንስ 25224 በጥቅሉ 48375 ተማሪዎች በ111 ፈተና መስጫ ጣቢያዎች በ4 ዙር የሚሰጥ ሲሆን በተፈጥሮ ሳይንስ 1ኛ ዙር ሰኔ 23፣24 እና 25 እንዲሁም 2ኛ ዙር ሰኔ 26፣27 እና 30 በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ በ1ኛ ዙር ሐምሌ 1፣2 እና 3 እንዲሁም 2ኛ ዙር ሐምሌ 4፣7 እና 8 እንደሚሰጥ ቀደም ሲል በወጣ ፕሮግራም መገለጹ ይታወቃል።
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት ማሰፈንጠሪያውን ይጫኑ!
https://linktr.ee/aacaebc