
Addis Ababa Education Bureau
June 20, 2025 at 09:30 AM
በከተማ አስተዳደሩ የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና እንዲካሄድ በቂ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወናቸው ተገለጸ።
(ሰኔ 13/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በየደረጃው ከሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አመራሮች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችና መምሪያ ኃላፊዎች፣ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ አመራሮች እንዲሁም ከደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች ፣ በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ጋር በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ለማስፈጸም በተዘጋጀ የጸጥታ እቅድ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በከተማ አስተዳደሩ የሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወን በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሩ አመራሮችና አባላት እያደረጉ ለሚገኘው የማይቋርጥ ድጋፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ምስጋና አቅርበው ዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማ ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በኦላይን የሚሰጥ በመሆኑ ፈተና መስጫ ጣቢያዎች ላይ የሚሰጠው ፈተናው በሁሉም ጣቢያዎች ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲሰጥ ከጸጥታ አካላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በከተማ አስተዳደሩ የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ያለምንም የጸጥታ ስጋትም ሆነ ሌሎች የፈተናውን ሂደት ከሚያውኩ ተግባራት ተጋላጭነት በጸዳ መልኩ እንዲካሄድ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የፖሊስም ሆነ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሩ አባላት በፈተናው ሂደት ተገቢውን የጥበቃ ፣ ፍተሻ እና እጀባ ተግባራትን በማከናወን ፈተናው ከማንኛውም የጸጥታ ስጋት ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚሽነር ጌቱ አርጋው አስታውቀዋል።
መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት ማሰፈንጠሪያውን ይጫኑ!
https://linktr.ee/aacaebc
