
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
June 12, 2025 at 02:17 PM
ሰኔ 5 2017
በሰላም እጦት ምክንያት ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ገራዶ አካባቢ ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች በድንገት መኖሪያችን እየፈረሰ ነው እኛም ለዳግም መፈናቀል ልንዳረግ ነው ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ፡፡
የደሴ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ እስካሁን ልቀቁ እንዳልተባሉና መፍትሄ ሳያገኝ እንደማያስነሳቸው ተናግሯል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ አካባቢ በነበረ የሰላም እጦት ምክንያት ቀያቸውን ለቀው የወጡ ከ700 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ከሶስት አመት በላይ በደቡብ ወሎ ዞን ገራዶ ተብሎ በሚጠራ ቦታ መጠለያ ተሰጥቷቸው እየኖሩ እንደነበር ነግረውናል፡፡
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ተጠልለው የሚኖሩበት መጠለያ ለባለሀብት ተሽጧል በሚል ምክንያት ካለምንም ምትክ ቦታ ሜዳ ላይ እየወጣ ነው የሚሉት ተፈናቃዎቹ እስካሁን ሶስት አባዎራዎች ተጠልለውበት የነበረ የሸራ ቤት ፈርሷል ይላሉ፡፡
ከዚህ በፊት ቦታው ለባለሃብት ተሽጧል ትነሳላችሁ የሚል ጭምጭምታ ብንሰማም ማንም ሰው ወደኛ መጥቶ ህጋዊ በሆነ መንገድ አልነገረንም ነበር ሲሉ ተፈናቃዮቹ ያስረዳሉ፡፡
አሁን ግን በድንገትና ባልጠበቅነው ሁኔታ ህፃናት፣ ነፍሰጡር እናቶች ፣ አካል ጉዳተኞችና አዛውንቶቹን ይዘን ሜዳ ላይ ልንቀረው ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ነግረውናል፡፡
ለደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት ስለ ጉዳዩ ብናሳውቅም መፍትሄ መስጠት የምንችለው የምግብ ችግር ቢሆን ነው ሲሉ መልሰውልናል፡፡
እኛም በደሴ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ቃሲም አበራን ጠይቀናቸዋል፡፡
እሳቸውም መሬቱ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ለአንድ ባለሀብት እንደተሰጠ በፍቃዱ ተፈናቃዮች እንዲኖሩበት እንደሰጣቸውና አሁን ወደ ስራ መግባት ስለፈለገ እንዲለቁ መጠየቁ ነግረውናል፡፡
ለተፈናቃዮች ተቀያሪ መጠሪያ ሳይመቻችላቸው እንደማይነሱም አቶ ቃሲም ለሸገር ተናግረዋል፡፡
ማርታ በቀለ
https://tinyurl.com/3ssraaa8