
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
June 12, 2025 at 02:18 PM
ሰኔ 5 2017
የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት ያጣነው ሃይማኖትን ከፖለቲካ ፖለቲካን ከሃይማኖት ስለምንቀላቅል ነው፡- አቡነ አብርሃም
በግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ከመጣፋፋት ይልቅ ወደ ሰላም እንዲመጡ የሃይማኖት አባቶች ተማፅነዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የእርስ በእርስ ጦርነቶችና ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ጥሪያቸውን የሚያቀርቡት የሃይማኖት አባቶቹ ዛሬም ድረስ የቀጠለው ግጭት እዲያበቃ እየተማፀኑ ነው፡፡
በባህር ዳር ከተማ በተሰናዳው ሶስተኛው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ኮንፈረንስ የሃይማኖት አባቶቹ ይህንኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው መርሃ ግብር ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም "ለገጠመን የሰላም እጦት መነሻው ጠባጫሪ ንግግር ነው ፣ከዚህ እንቆጠብ ያሉት ሊቀ ጳጳሱ ምንም እንኳን መሰል የሰላም ጥሪዎችን ስናስተላልፍ ብንከርምም ተሰሚነት አጥተናል "ብለዋል፡፡
"ይህም የሆነው እኛ የሃማኖት አባቶች ሃይማኖትን ከፖለቲካ ፖለቲካን ከሃይማኖት እየቀላቀልን ህዝቡን ግራ በማጋባታችን ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"በግጭት ውስጥ በግራና ቀኝ የተሰለፋችሁ ልጆቻችን የሰላም ጥሪያችንን ተቀብላችሁ ወደ መነጋገር እንድትመጡ" ሲሉም ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተማጽነዋል፡፡
በተጨማሪም በመድረኩ ተገኝተው የሰላም ጥሪያቸውን ያስተላለፉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንትና የሃማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለዘመናት ሲፈትናት የቆየው የደህንነት ማጣትና ድህነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አፈሙዝን እያስቀደሙ ወደ ስልጣን የሚመጡ ፖለቲከኞች የደህንነታችን ስጋት ሆነው ቆይተዋል፤በዚህም ምክንያት አንዱ የሰራውን ሌላው ስለሚያፈርስ በድህነታችን ቀጥሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"ፈተናችን እንዲያበቃ ወደ መነጋገር መሸጋገር አለብን እዚህ ላይ እንበርታ" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አቢያተ ክርስቲናት ካውንስል ጠቅላ ፀሃፊ ቄስ ደረጀ ጀምሩ ጦርነት እንደ ሃገር አድቅቆናል ከዚህ በላይ የሚያስከትለውን ጉዳት የመሸከም አቅም አይኖረንምና ጦርነት፣ግጭት፣አለመግባባት በቃን እንበል፤ሰላም ህዝቡ ሰላንም ተርቧል፤እያሳለፈው ካለው ሰቆቃ እናሳርፈው ሲሉ እርሳቸውም በሁሉም ወገን ያሉ ተፋላሚዎችን ወደ ሰላም ኑ ሲሉ ተማፅነዋል፡፡
ምንታምር ፀጋው
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ.
https://tinyurl.com/3j5cw5wj