
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
June 14, 2025 at 08:45 AM
ሰኔ 7 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
#ኢራን
ኢራንም በእስራኤል ላይ የብቀላ አፀፋ እየሰነዘረች ነው፡፡
እስራኤል ቀደም ሲል በኢራን የኒኩሊየር ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ያለችውን ከባድ ድብደባ መፈፀሟን አልጀዚራ አስታውሷል፡፡
የኢራን ሹሞች በእስራኤል ድብደባ 78 ሰዎች ተገድለውብናል ብለዋል፡፡
ከመካከላቸውም ስመ ጥር የጦር መኮንኖች እና ከ6 ያላነሱ የኒኩሊየር ሊቃውንት መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ኢራንም በምላሹ ሌሊቱን ወደ እስራኤል ባልስቲክ ሚሳየሎችን መተኮሷን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የኢራንን የሚሳየል ተኩስ ተከትሎ በኢየሩሳሌም ከባድ ፍንዳታ እንደተሰማ እና በቴል አቪቭ ደግሞ ከባድ ጭስ ሲትጎለጎል መታየቱ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
ግጭቱ ከእለት ጥቃትም እየተሻገረ መጥቷል ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሁለቱም አገሮች ከግጭት አባባሽ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጥሪ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡
#ኬንያ
በኬንያ በፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ሕይወቱ አልፎ በተገኘው ወጣት ግድያ የተጠረጠሩ የናይሮቢ ከተማ ዋነኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ተይዘው ታሰሩ፡፡
ሌላ የፖሊስ መኮንን እና የጣቢያው ቴክኒሺያንም በጥርጣሬ መያዛቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ቴክኒሺያኑ በጥርጣሬ የተያዘው የወጣቱ ሕይወት ባለፈበት ወቅት የጣቢያውን የደህንነት መከታተያ ካሜራ እንዳይሰራ በማድረጉ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
በፖሊስ ጣቢያ በተያዘበት ሕይወቱ አልፎ በተገኘው ወጣት የድረ ገፅ የመጣጥፍ አቅራቢ ምክንያት ሕዝባዊ ቁጣው አልቀዘቀዘም ተብሏል፡፡
በዚሁ ጉዳይ በናይሮቢ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ኬኒያውያን ከፍተኛ የፖሊስ ሹሞችም ሀላፊነታቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸውን የፃፈው ደግሞ አናዶሉ ነው፡፡
ገለልተኛ የፖሊስ ተግባራት ተከታታይ አካልም ጉዳዩን በብርቱ እየመረመረው ነው ተብሏል፡፡
#ሱዳን
የአለም የጤና ድርጅት በሱዳን ከተቀሰቀሰ የቆየው የኮሌራ ወረርሽኝ ወደ ጎረቤት አገሮችም ሊዛመት ይችላል ሲል አስጠነቀቀ፡፡
በአሁኑ ወቅት የኮሌራ ወረርሽን ከሱዳን 28 ግዛቶች በ13ቱ እየተዛመተ እና አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን ሬውተርስ ፅፏል፡፡
የጤና አጠባበቅ እና የንፅህና መጓደል ለወረርሽኙ መባባስ ዋናው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር እና የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ከ2 አመታት በላይ በጦርነት ላይ ናቸው፡፡
ጦርነቱ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለስደት እና መፈናቀል የሚዳርጋቸው ሰዎች ብዛት እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በየመጠለያው ተፈናቃዮች በተፋፈገ ሁኔታ የሚኖሩ መሆኑ ለወረርሽኑ መዛመት ሌላኛው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
በሽታው የሱዳንን ስደተኞች ወዳስጠለሉ አገሮችም ሊዛመት እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅት ማስጠንቀቁ ተሰምቷል፡፡
#ደቡብ_አፍሪካ
በደቡብ አፍሪካ የሰሞኑ ጎርፍ የገደላቸው ሰዎች ብዛት እየጨመረ ነው ተባለ፡፡
በጎርፍ የተወሰዱ የተጨማሪ ሰዎች አስከሬን መገኘቱ እንደቀጠለ አናዶሉ ፅፏል፡፡
እስካሁንም በጎርፉ የሞቱ ሰዎች ብዛት 67 መድረሱን ግዛታዊ ሹሞች ተናግረዋል፡፡
የምስራቃዊ ኬፕ ግዛት የጎርፍ አሉታዊ ተፅዕኖ ያየለበት ነች፡፡
በግዛቲቱ ከባድ ጎርፍ ያጋጠመው ሲጥል በነበረው ዶፍ ዝናብ እንደሆነ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
የክዋዙሉ ናታል ግዛትም የጎርፍ አደጋው ሰለባ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il