ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
June 16, 2025 at 03:42 PM
ሰኔ 9 2017 በረቂቅ ደረጃ ያለው አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ኪሳራን የሚያስመዘግቡ ድርጅቶችን ከ #ግብር_ነፃ የሚያደርገውን የቀደመውን አዋጅ ድንጋጌ መሻሩ አከራካሪ ሆኗል፡፡ አዋጁ ካካተታቸው ድንጋጌዎች መካከል ኪሳራ የሚያስመዘግቡ ግብር ከፋዮች ኪሳራ ውስጥ ቢሆኑም እንኳን የዓመታዊ ገቢያቸውን 2.5 በመቶውን በግብር መልክ መክፈል እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡ ከዚህ ቀደም ተጀምሮ ብዙም ሳይሰራበት የቀረው ዝቅተኛ የግብር አማራጭ በአዲሱ አዋጅ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለ ሲሆን በዚህም በዝቅተኛ የግብር አማራጭ መሰረት ኪሳራ ውስጥ መሆናቸውን የሚያሳውቁ ድርጅቶች ዝቅተኛውን የ2.5 በመቶ ግብር ይከፍላሉ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ማሻሻያ ምክንያቱ ግብር ለመክፈል ከተመዘገቡ ግብር ከፋዮች በትክክል ግብር የሚከፍሉት 37 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው፤ በኪሳራና በሌሎችም ምክንያቶች ቀሪ 63 በመቶዎቹ ግብር እንደማይከፍሉ በጥናት ደርሼበታለሁ ያለው ረቂቁን ያሰናዳው የገንዘብ ሚኒስቴር እነዚህን ለማስከፈል ያለመ ነው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ነባራዊው ሃቅ የሚያሳየውም ሆን ብለው የኪሳራን ሪፖርት አድርገውና ስም ቀይረው በሌላ ስራ ላይ የሚሰማሩ ግለሰቦች ስለመኖራቸው እንደሚስማሙ ነግረውናል፡፡ ይሁንና እነርሱን ግብር ለማስከፈል ሲባል የተጨመረው ድንጋጌ ኪሳራ ተፈጥሯዊ መሆኑን የዘነጋ፤መክሰር አይቻልም የሚል አዝማሚያ ያለው ነው፤ ከዓመታዊ ገቢያቸው መክፈል አለባቸው የተባለው 2.5 በመቶ በጣም የበዛ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ በረቂቁ መካተት ያለበት አንድ ድርጅት ያቀረበውን የኪሳራ ሪፖርት መሰረት አድርጎ ድርጅቱ መክሰር አለመክሰሩን የሚያጣራ፤ ’’በገለልተኛ አጣሪ ቡድን ተጣርቶ ውሳኔ ይሰጥበታል’’የሚል ድንጋጌ መካተት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡ ኪሳራ ተፈጥሯዊ እንደሆነ የሚናገሩት ሌላው ባለሙያ አቶ ዮሃንስ ሽፋ ናቸው፡፡ እርሳቸው በሂሳብ ስራና ድርጅቶችን በማማከር ለረጅም አመታት በዘለቀው ስራ ልምዳቸው ከግብር ለመሸሽ የኪሳራ ሪፖርት የሚያቀርቡ እንዳሉ ይታወቃል ይላሉ፤ይሁንና እነርሱን መከታተያ መንገድ የሚያበጅ አንቀፅ ሊካተትበት ይገባል፤ ይህ ካልሆነ ግን በረቂቁ የሰፈረው ሊያሰራ አይችልም፤ከዚህ ይልቅ የቀደመው አዋጅ ኪሳራን ለ5ዓመታት ማሸጋሸግ የሚያስችል በመሆኑ የተሻለ ነበር ብለውናል፡፡ የሚወጡ አዳዲስ ህጎችና ድንጋጌዎች መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ መሆን አለበት የሚሉት የሂሳብ ባለሙያውና አማካሪው አቶ ዮሃንስ እዚህም እዚያም ባለው የሰላም እጦት እንደልብ በማሰራበት ሃገር ባትሰራም፣ ባታተርፍም ግብር ክፈለኝ ማለት ከእውነት ጋር መፋታት እንደሆነና፤የንግድ ስራውንም ይሁን ኢኮኖሚውን በእጅጉ እንደሚጎዳው ጠቅሰዋል፡፡ ነጋዴው በእርሱ ላይ የሚወድቀውን እያንዳንዱ ጫና የሚያሸጋግረው ለማህበረሰቡ በመሆኑ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ይሆናል የሚል እምነትም አላቸው፡፡ የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ በበኩላቸው በአዲሱ የገቢ ግብር የአዋጅ ማሻሻያ መካተት አለበት ያሉትንም ሲናገሩ ግብር የሚሰውሩ ግለሰቦችን የህግ ተጠያቂ ማድረግና በገንዘብ መቅጣት በቂ አይደለም ንብረታቸው ይወረስ የሚል መካተት አለበት፤ለውጥ የሚመጣው በዚህ መንገድ ነው ብለዋል፡፡ በመሻሻል ላይ ያለው አዋጅ መንግስት የታክስ መሰረቱ በማስፋት የሚሰበስበውን ግብር ለመጨመር፤ከግብር የሚሸሹትን ወደ ስርዓቱ ለማስገባት ያለመሆኑን ከረቂቁ መመልከታቸውን የነገሩን ባለሙያዎቹ ከመፅደቁ በፊት መጤን አለባቸውን ያሉትንም አስረድተዋል፡፡ በዚህም መንግስት ሰዎች በሰሩት ልክ ግብር እንዲከፍሉ ለማድረግ የሚበረታውን ያህል ሰዎች ምን አይነት አሰራር ብከተል ነው፤ ሰዎች በቀላሉ ስራ ሰርተው መኖር የሚጠበቅባቸውን መክፈል የሚችሉት የሚለውን ቢፈትሽ፤ህጉ ሲሻሻል ስራን የሚያቀልል ወይስ ማህበረሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥር ነው ሚለውንም ማጤን ይገባዋል የሚል ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ… https://www.mixcloud.com/ShegerFM/gftnjgnmjy/ ምንታምር ፀጋው የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… 📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1 📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX 📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s 📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il

Comments