
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
June 18, 2025 at 11:57 AM
ሰኔ 11 2017
በአዲስ አበባ የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን በተለይም የእግረኞችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚሰሩ የፍጥነት ማብረጃዎች ደረጃቸውን ጠብቀው መሆን አለበት ያለበለዚያ ለተጨማሪ አደጋ የሚጋብዙ ይሆናሉ ተባለ፡፡
በየጊዜው ተከታትሎ መንገዶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጥገና እንደሚደረግላቸው ሁሉ እነርሱም መታደስ ይሻሉ ተብሏል።
በከተማዋ አደጋ ይደጋገምባቸዋል በሚባሉና በተመረጡ አካባቢዎች በተለይ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚሰሩት የፍጥነት ማብረጃዎች (speed breakers) ያን ያህል የዲዛይንም ይሁን የግንባታ ችግር ባይታይባቸውም በየአካባቢው በተለይ በመንደሮች ውጥ የሚሰሩት ግን በድጋሚ ሊታዩ እንደሚገባና የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የፍጥነት ማብረጃዎች የተሽከርካሪ አደጋን በመቀነስና የእግረኞችን ደህንነት ማስጠበቅ ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ጥያቄ ባይኖረውም የግንባታ ደረጃቸው ግን በአግባቡ መሆን አለበት የሚሉት በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ደህንነት ላይ የሚሰራው የብሉምበርግ አስተባባሪው አቶ ዮሐንስ ለገሰ ናቸው፡፡
የፍጥነት ማብረጃዎቹ ከተገነቡ በኋላ በየጊዜው ክትትል እየተደረገላቸው ጥገና የሚያሻቸውን መጠገን ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ዮሐንስ በከተማዋ በተጠና ጥናት ፍጥነት ማብረጃዎች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ የሚደርስ የአደጋ መጠን መቀነሱን ነገር ግን በአግባቡ መሰራታቸው እና በተለይ የጥራቱን ጉዳይ ማስተካከል ላይ ግን ክትትል ይፈልጋሉ ብለዋል።
ከፍጥነት ወሰን ቁጥጥር ጋር በተያያዘ በኃላፊነት የሚሰራውና የፍጥነት መቀነሻዎቹን የሚገነባው የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ስለ ጉዳዩ ምን ይላል ስንል ጠይቅናል፡፡
አቶ አማረ ታረቀኝ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው የፍጥነት መቀነሻዎቹ በተገነቡባቸው ቦታዎች ላይ የአደጋ መጠኑ መቀነሱንና የእድሳቱን ጉዳይ ከመንገዶች ባለስልጣን በመሆን ለማስተካከል እንሰራለን ብለዋል፡፡
ሁሉም ቦታዎች ላይም የፍጥነት መቀነሻዎች እንደማይገነቡና አንዳንድ ቦታዎች ላይ በራዳርና ካሜራ በመታገዝ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ በተለይም በእግረኞች ላይ ከፍጥነት ጋር የሚደርሱ የትራፊክ አደጋችን ለመቀነስ የፍጥነቱን በመገደብ እና በተለዩ ቦታዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ተናግሯል፡፡
ሙሉ ዘገባውን በድምጽ ያድምጡ…. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/fxtgnhjtrfjfttrhy/
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il