ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
June 19, 2025 at 08:48 AM
ሰኔ 12 2017 ብሔራዊ ባንክ በገለልተኛ የሒሳብ መርማሪ ተቋም ኦዲት የተደረገ ዓመታዊ የሀብት እንቅስቃሴውን የሚሳይ ዳጎስ ያለ ሰነድ ይፋ አድርጓል፡፡ ሰነዱ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ ገበያው የተረጨው አዲስ የገንዘብ መጠን በ200 በመቶ ማድረጉን አሳይቷል፡፡ #ብሔራዊ_ባንክ ባለፉት 5 ዓመታት ለገንዘብ ሚኒስቴር የሰጠው 700 ቢሊየን ብር የቀጥታ ብድርም ዋጋ ግሽበት ካስከተሉ መንስኤዎች አንዱ መሆኑ ሰምተናል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት የበጀት ጉድለቱ ሰፍቶ ወጭውን ለመሸፈን ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ ብድር በመቶ ቢሊዮኖች እንዲወሰድ ያስገደዱት ሁነቶችም ተፈጥረው ነበር ተብሏል፡፡ የሰሜኑ ጦርነት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ እና በሩስያ ዩክሬይን ጦርነት ምክንያት የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መጨመር መንግስትን ከፍተኛ ወጪ የጠየቁት ሁነቶች እንደነበሩ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የፋይናንስ ባለሙያው አቶ መርዕድ ፍቅረዮሀንስ አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በቀጥታ ብድር ከብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ሚኒስቴር የወሰደው ከፍተኛ ብድር ባለፉት አምስት አመታት በገበያው ውስጥ የገንዘብ ፍሰቱ በሁለት እጅ ያህል እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በገበያው ውስጥ ይገላበጥ የነበረው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን አንድ ትሪሊዮን ብር ነበር ብለዋል ባለሙያው፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ እስካለፈው የፈረንጆቹ አመት የሰኔ ወር ድረስ የገንዘብ ፍሰቱ ወደ ሁለት ነጥብ ሰባት ትሪሊዮን ብር ማደጉን ሰነዱን ጠቅሰው ነግረውናል፡፡ ይህም ለዋጋ ግሽበትና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማጋለጡ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲደረግም አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠሩን ሰምተናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ገበያው የፈሰሰውን ከፍተኛ ገንዘብ መልሶ ለመሰብሰብ የወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ውጤት አምጥተውለታል ተብሏል፡፡ እየተገባደደ ያለው በጀት ዓመትም መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ከብሔራዊ ባንክ የቀጥታ ብድር ያልወሰደበት ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ሙሉ ዘገባውን በድምጽ ያድምጡ…. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/ynhjdt/ ትዕግስት ዘሪሁን የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… 📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1 📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX 📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s 📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il

Comments