
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
June 20, 2025 at 04:47 PM
ሰኔ 13 2017
በተፈጥሮ እንዲሁም ከጊዜ በኋላ በሚያጋጥሙ ጉዳቶች በዐይን ብሌን ላይ በሚደርስ ጠባሳ ብርሃናቸውን ለተነጠቁ ሰዎች በጎ ፈቃደኞች በሕይወት እያሉ በሚገቡት ቃል የብዙዎች ብርሃን ተመልሷል፣ ዳግም ማየት ችለዋል፡፡
ይህ ስራ በኢትዮጵያ ከተጀመረ ዓመታት አስቆጥሯል።
በብሌን ጠባሳ ምክንያት የተከሰተ አይነ ስውርነትን ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሽ በተገኘ የዐይን ብሌን በመተካት ጉዳቱ የገጠማቸው ሰዎች ዳግም ወደ ትምህርት እና ስራ ተሰማርተው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከጊዜ በኋላ የዐይን ብርሃኑን ያጣውና ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሽ በተገኘ የዐይን ብሌን ብርሃኑ የተመለሰለት ወጣት ስለ ዓይን ብሌን ልገሳው ይናገራል፡፡
የብሌን ንቅለ ተከላው ከተደረገለት በኋላ መስራትና ትምህርቱን መቀጠሉን የሚናገረው ወጣቱ በበጎ ፈቃድ ብቻ በሚደረግ ልገሳ የብዙዎችን ብርሃን መመለስ ይቻላል፤ ለዚህም ተደራሽ ለመሆን ማንኛውም ማህበረሰብ ብሌኑን ከህልፈት በኋላ ለመለገስ ቃል መግባት አለበትም ይላል፡፡
ስለተደረገላቸው በብዙ እንደሚያመሰግኑና አሁን ላይ ሰብሰብ ብለው ማህበር በማቋቋም ግንዛቤ ላይ የሰሩ መሆኑንም ወጣቱ ይናገራል፡፡
የበለጠ ይሄንን ግንዛቤ ለመፍጠር ማህበር በማቋቋም ከኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብሏል፡፡
በ11 ወራት ውስጥ ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች ከሕልፈት በኋላ ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውን የሚናገሩት የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ ባንክ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ሀብታሙ ታዬ ይህ ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበሩት አኳያ የተሻለ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው ሰዎችም ወደ 315 መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከለጋሾች የሚገኝ የብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና የሚሰጡ በክልሎች 4 ሆስፒታሎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ ነገር ግን በሀገር ደረጀ ያለው የአይን ባንክ አንድ አዲስ አበባ ላይ ብቻ መሆኑን ከዚህ በላይ እናዳንሰራ አድርጎናል፤ ተጨማሪ የዓይን ባንክ በክልሎች ለማቋቋምም እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ ስር የሚገኘው የአይን ባንክ የብሌን ንቅለ ተከላ የሚያደርጉ ባለሙያዎቹ ቁጥር አጠቃላይ ለሀገሪቱ 12 ብቻ መሆናቸውን የተነገረ ሲሆን የባለሙያዎቹን ቁጥርና የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ግብዓቶችን ማሟላት ላይ በብዙ መስራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት ብርሃናቸውን ማጣታቸውንና አገልግሎቱን እንደሚጠባበቁ ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….. https://www.mixcloud.com/ShegerFM/fhttf/
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il