ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
ShegerFM 102.1(ሸገር 102.1)
June 21, 2025 at 04:20 PM
ሰኔ 14 2017 የአፍሪካ ሀገራት መንግስታት ለዜጎቻቸው የሚሰጡትን አገልግሎት ለማሻሻል የሚቀይሱት ስትራቴጂ፤ በአብዛኛው ውጤታማ አይሆንም ተባለ። ይህ የተባለው 10ኛው የአፍሪካ ሲቪስ ሰርቪስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በተጀመረው  የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤ ላይ ነው። ሁሉም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ተሳታፊ በሆኑበት በዚህ ጉባኤ በአፍሪካ ሃገራት የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ምን መልክ አለው? በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይትም ተደርጎበታል። ሀገራቱ ያላቸው የእድገት ደረጃ ተቀራራቢ መሆኑን ተከትሎ በየሀገራቱ መንግስታት ለዜጎቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት በአብዛኛው ኋላቀርና አካባቢዎቹ ከመሃል ሃገር ራቅ ባሉ ቁጥር አገልግሎት አሰጣጡም ደካማ የሚሆንበት መሆኑ ታይቷል ተብሏል። ለዚህ ደግሞ ሃገራቱ ለረጅም ዓመታት በቅኝ ግዛት ውስጥ በመቆየታቸው የመንግስት አገልግሎቶቹም በቅኝ ገዢዎቹ እጅ የነበሩ በመሆናቸውና ከተረከቡም በኋላ ማዘመን አለመቻላቸው፤ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ አገልጋይ የሆኑ መሪዎችን ማጣትና ሌሎችም ምክንያቶች መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል። በጥናታዊ ፅሁፉ እንደተብራራው አፍሪካ በታሪክ አጋጣሚ  በገጠሟትና እስካሁንም መፍታት ባልቻልቻቸው ችግሯቿ ምክንያት ዜጎቿ የመንግስትን ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት አልታደሉም። ይህንን ለማስተካከል በየሃገራቱ በየጊዜው የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ማሻሻያ ስትራቴጂ ይነደፋል፤ ለማስፈፀም ተብሎም ረብጣ ገንዘብ ይመደባል፤ ይሁንና አንዱም ችግር ሳይፈታ ስትራቴጂው በወረቀት ላይ እንዳለ እንደሚቀር የየሃገራቱ ተወካዮች በውይይቱ ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ሃገራቱ የሚሞክሯቸው አገልግሎትን የማዘመን ሙከራዎች ፍሬ የሚያፈሩበት ሁኔታ መኖሩ ተነግሯል። መሰል ሙከራዎች እንዲበረቱ የሃገራቱ መንግስታት በአሁኑ ወቅት ብዙ ለውጥ እየታየበት ያለውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ፤ መንግስታት የዜጎቻቸውን የልብ ትርታ እያደመጡ የፍላጎታቸውን እንዲሞሉ፣ በሚሰጡት አገልግሎት የሰዎችን እርካታ የሚለኩበት አሰራር እንዲዘረጉ፣ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነ አገልግሎት ለዜጎቻቸው እንዲሰጡ ተጠይቋል። ይህ ሲሆን አፍሪካዊያን የሚመኙትን ቀልጣፋና ዘመኑ የሚጠይቀውን አገልግሎት ከየሃገሮቻቸው ማግኘት ይችላሉ ተብሏል። ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት በሚዘልቀው   10ኛው የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤ ኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለማዘመን እየከወንኩ ነው ያለችውን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ እያስረዳች ነው። በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተጀመረው በዚህ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ስለ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሲያብራሩ በርከት ያሉ የመንግስት አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የቀለጠፈ አገልግሎቾችን የሚሰጡበት፤ በየትኛውም ጥግ ያለ ዜጋ አገልግሎት የማይጎድልበት መሆኑን የምናሳይበት ነው ብለዋል። ከጉባኤው በተጨማሪ በህብረቱ ቅጥር ግቢ ዘመኑ የደረሰበትን አገልግሎት እየሰጠን ነው ያሉ የሃገር ውስጥ እና ከአፍሪካ ሃገራት የመጡ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ስራዎቻቸውን የሚያሳዩበት አውደ ርዕይም ተከፍቷል። ምንታምር ፀጋው የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… 📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1 📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX 📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s 📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il

Comments