Meseret Media
Meseret Media
June 5, 2025 at 02:39 PM
#የምርመራዘገባ የ63 ዓመቱ አዛውንት እንዴት እና ለምን ተገደሉ? (ይህ ዜና ግንቦት 24/2017 ዓ/ም ቀን ለመሠረት ሚድያ ከፋይ አባሎች 'paid subscribers' ቀርቦ የነበረ ነው) (መሠረት ሚድያ)- ከቅርብ ግዜ ወዲህ በርካታ ዜጎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ሀይሎች በጭካኔ ሲገደሉ፣ ሲታገቱ፣ ደብዛቸው ሲጠፋ እና ሲታሰሩ መስማት የእለት ተእለት ክስተት ሆኗል። ይህን ማሳያ ይሆን ዘንድ መሠረት ሚድያ ዛሬ ከተገደሉ ስድስት ወር የሞላቸውን የ63 አመቱን የአቶ ከፋለ በላይን ታሪክ እናቀርባለን። ድርጊቱ የተከሰተው የዛሬ 6 ወር ነው፣ ቦታው ደግሞ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ማቻከል ወረዳ፣ አማኑኤል ከተማ፣ 'ጎጃም ዱር' የሚባለው አካባቢ ነው፡፡ አቶ ከፋለ ቤት ፊት ለፊት በሚገኝ አንድ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የመከላከያ ካምፕ አለ፣ ወታደሮች የቤተክርስቲያኑን አዳራሽ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ከዚህ ካምፕ ውስጥ አንድ የመከላከያ አባል እቃ ለመግዛት በግምት ከአቶ ከፋለ ቤት በ70 ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ አንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ በሚመጣበት ጊዜ በታጠቁ ኃይሎች ይገደላል፡፡ በዚህ የተበሳጩ የመከላከያ አባላት የሟች ጓደኛቸውን አስከሬን አንስተው ከወሰዱ በኋላ እንደገና ተመልሰው በመምጣት ያንን የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ በእሳት እንዳያያዙት የአይን እማኞች ይናገራሉ። "ይህ ሁሉ ሲሆን አቶ ከፋለ ምንም አይነት መረጃ አልነበራቸውም፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ጎረቤት ቤታቸው ድረስ ሄዳ መብራቱ የተሳበው ከእሳቸው ቤት ስለነበር እሳት ስለተነሳ ቆጣሪውን አጥፉልን ትላቸዋለች፣ እሳቸውም በድንጋጤ ቆጣሪውን አጥፍተው እሳቱን ሊያጣፌ ሄዱ" የሚሉት ጉዳዩን በወቅቱ የታዘቡ ሰዎች ናቸው። "በዚህ መሀል እሳት ለማጥፋት የወጡትን ሰዎች ሰብስበው ወስደው አሰሯቸው፡፡ ካሰሯቸው ሰዎች መካከል የተወሰኑትን የለቀቋቸው ቢሆንም አቶ ከፋለ በላይ እና አቶ ተስፋዬ የተባሉ ሌላ ግለሰብን ለይተው በማስቀረት ወስደዋቸዋል" በማለት ድርጊቱን ያስረዳሉ። መሠረት ሚድያ በስፍራው ከነበሩ ሌሎች ምንጮቹ ማረጋገጥ እንደቻለው ወታደሮች ሁለቱን ግለሰቦች በድብደባ ክፉኛ ካሰቃዩዋቸው በኋላ ግድያ ፈፅመውባቸዋል፣ አስከሬናቸውንም እስካሁን ድረስ የት እንዳለ አይታወቅም። "አንድ ቀን ተሳክቶልኝ አሳርፍሀለሁ፣ እኔም ህልሜን አሳካለሁ ብዬ ሁሌ እንደተመኘሁኝ እና እንደተጨነቅሁኝ አንተንም ሳላስደስትህ የራሴንም ኑሮ ሳልኖር ባላሰብሁት ሰዓት እና ሁኔታ አባቴን ገደሉብኝ" የሚለው ልጃቸው ሰማ ከፋለ ሀዘኑ ፍፁም ሊቀበለው የማይችለው እንደሆነበት ይናገራል። "አባቴን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ሀቀኛ እና እውነተኛ እና የዋህ ነው፣ ገና በማለዳው መሬቱ በግፍ በመወሰዱ ለፍቶ፣ ጥሮ፣ ግሮ ነው ልጆቹን ያሳደገውና ያስተማረው። ለራሱ አልኖረም ነበር፣ አርፎም አያውቅም ነበር" የሚለው ልጃቸው ነው። አክሎም "አባቴ ይህ በፍፁም አይገባውም ነበር፡፡ ያደረገው ነገር ጥፋት ቢሆን እንኳን አስሮ፣ አስተምሮና አስጠንቅቆ መልቀቅ ይቻል ነበር፡፡ አባቴ ፍትህ እንዲያገኝ ሊረዳኝ የሚፈልግ የመንግስትም ይሁን የግል የፍትህ አካል ወይም የመብት ተሟጋች ካለ ሊያወራኝ ይችላል" ብሏል። መንገድ ላይ ባለ ችግር ምክንያት ዛሬ ለስድስት ወር መታሰቢያው እንኳን ቦታው ላይ መገኘት እንዳልቻለ የሚገልፀው ልጃቸው ሰማ 'በህይወት እንዳለሁ አልቆጥረውም" ብሏል። የአቶ ከፋለ ቤተሰቦች አስከሬን እስካሁን ድረስ እንዳልተሰጣቸው እና ከሶስት ወር በላይ ከደብረ ማርቆስ እስከ ብርሸለቆ ሄደው እንደፈለጉ ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል። "አንዳንዱ አንዴ እዚህ ነው፣ አንዴ እዛ ነው የታሰረው ይላል። ነገር ግን ከውስጥ በተገኘ መረጃ እና በተዘዋዋሪ እንዲደርስን በተደረገ መረጃ መሠረት በታሰሩ ሰሞን ነው የተገደሉት፣ ምናልባት በአንድ ወይም በሁለት ቀን ውስጥ። ትንሽ ከተማ ስለሆነ ማን ምን እንደተደረገ ወሬው ይወጣል። የሟቾች ዝርዝር ውስጥም ስማቸው እንዳለ መረጃ ደረሰን" በማለት የአቶ ከፋለ ልጅ ተናግሮ በዚህም መሠረት ለቅሶ እንደተቀመጡ አስረድቷል። መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ መረጃ ለመጠየቅ የመከላከያ ሰራዊት ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ኮ/ል ጌትነት አዳነን ለማናገር ያረገው ሙከራ አልተሳካም። መረጃን ከመሠረት! ***የምናወጣቸውን መረጃዎች በእለቱ ለማግኘት ከፋይ አባል (paid subscriber) ይሁኑ ⤵️ https://substack.com/@meseretmedia
😢 2

Comments