
Ahadu Radio And Television
June 13, 2025 at 04:58 PM
*ተፈናቃዮች ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ እየተደረጉ ነው ሲሉ በትግራይ ክልል የሚገኙ ፓርቲዎች ገለጹ*
ሰኔ 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የፌደራል መንግሥትም ሆነ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር "ተፈናቃዮችን ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያነት እየተጠቀሙ ነው" ሲሉ በክልሉ የሚቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
"የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ የቀድሞው የህወሓት አካል የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ፈንታ፤ ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያነት እያደረጓቸው ነው" ሲሉ የሳልሳ ወያኔ ሓርነት ትግራይና ባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲዎች አስታውቀዋል፡፡
"የትግራይን ሕዝብ ጥያቄ በፕሬቶሪያው ስምምነት ማነቆ ውስጥ በማስገባት የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ለራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚ ለመጠቀም እንጂ፤ የትግራይ ሕዝብን ከወንድምና እህት ጎረቤት ሕዝብ ጋር በጋራ አብሮ እንዲኖር ተገቢውን ሥራ እየሰሩ አይደለም" ሲሉ ለአሐዱ የተናገሩት የሳልሳይ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኔ አጽብዓ ናቸው ፡፡
“የፕሪቶሪያ ስምምነት የመሬት ማካለል አይደልም" ሲሉ የተናገሩት አቶ ብርሃኔ፤ "ነገር ግን ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት እንመለስ የሚል ነበር" ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
ሆኖም አሁን ባለው የትግራይ ክልል የፖለቲካ ውጥረት፤ ይህንን ማስፈጸም የሚቻልበት ዕድል በእጅጉ እየደበዘዘ በመሆኑ ስጋት ውስጥ የሚከት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"የትግራይ ሕዝብ ከአማራ፣ ከአፋርና ከኤርትራ ሕዝብ ጋር በድንበር ተጋርቶ ለረጅም ዓመታት አብሮ የኖረ ሕዝብ ነው" ሲሉ የተናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ "በተለየ መልኩ ከአማራ ክልል ጋር የተፈጠረው ፖለቲካዊ ውዝግ በሕዝብ ድምጽ ቢፈታ የተሻለ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል" ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር ክብሮም በርኸ በበኩላቸው ከላይ የተነሳውን ሀሳብ የሚጋሩት ሲሆን፤ "የቀድሞው ህወሓት ሥሙን ቀይሮ አሁን የጊዜው አስተዳደር የተባለውም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት የሕዝብ መሞትን፣ መፈነቀልና የትኛውንም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል እየሄዱበት ያለው እርቀት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም" ብለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ "አሁንም ቢሆን የትግራይ ችግር የኢትዮጵያ ችግር በመሆኑ፤ የክልሉ አመራሮችም ይሁን የፌደራል መንግሥቱ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
