
Ahadu Radio And Television
June 14, 2025 at 05:05 PM
*በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ መቆየት ካለባቸው ጊዜ በላይ ለረዥም ዓመታት የቆዩ 115 ሕጻናት እንደሚገኙ ተገለጸ*
ሰኔ 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሕጻናት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ መቆየት የሚችሉት እስከ 1 ዓመት ከ6 ወር ብቻ ቢሆንም ለረዥም ዓመታት የቆዩ 115 ሕጻናት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በክልል በሚገኙ 8 ማረሚያ ቤቶች ውስጥ 59 ወንድ እና 56 ሴት በድምሩ 115 ሕጻናት ከወላጆቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት እንደሚገኙ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ቤት ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ሕጻናት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በተቻለ መጠን በእንክብካቤ እንዲያድጉ እና ከውጭው ማህበረሰብ ጋር በትምህርት ቤቶች እንዲገናኙ እየተደረገ ቢሆንም፤ አሁንም ሙሉ ነው ማለት እንደማይቻል እንደማይቻል ኮሚሽነር አለማየሁ አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ "ሕጻናቱ ማረሚያ ቤት ውስጥ ከወላጆቻቸው ጋር ለሚቆዩበት የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም" ያሉ ሲሆን፤ "ሆኖም እድሜያቸው ከፍ ሲል ለአሳዳጊዎች እና ለተቋማት ለመስጠት ወላጆች ፈቃደኛ አይደሉም" ብለዋል፡፡
"ይህም ሕጻናቱ ለረጅም ጊዜ ማረሚያ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ እያደረገ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ይህንን ቢሉም የማረሚያ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀፅ 28 ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቆየት የሚችሉት ለአንድ ዓመት ከ6 ወር ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡
ሆኖም "በክልሉ በሚገኙት ማረሚያ ቤቶች እዚያው ተወልደውና በተለያየ የእድሜ ክልል ገብተው እየኖሩ የሚገኙ እስከ 14 ዓመት ድረስ የሆናቸው 115 ሕጻናት ይገኛሉ" ብለዋል፡፡
ይህን መሰሉ ጉዳይ በሌሎች ክልሎች በሚገኙ ማረሚያ ቤቶችም የሚስተዋል ሲሆን፤ "ሕጻናቱ በማረሚያ ቤት ለረዥም ጊዜ ሲቆዩ የሚደርስባቸውን ጫና ለመቀነስ እና የሥነ ልቦና ጉዳት እንዳያጋጥማቸው ለማድረግ ሕጉ ምን ይላል?" ሲል አሐዱ የሕግ ባለሙያ እና የኢትዮጵያ ሰራተኞች መብቶች ተሟጋች የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሌድ ጌትየን ጠይቋል፡፡
በ2020 በወጣ መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ በክልልም በከተማም ያሉት ሁሉም ማረሚያ ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን አፍሪካን ቻይልድ ፖሊሲ በጥናቱ አሳይቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ "ለሕጻናት ታስበው የሚገነቡ ማረሚያ ቤቶች ባለመሆናቸው ሕጻናቱ ችግር ላይ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡
"ሕጻናት ማረሚያ ቤት መቆየት ያለባቸው ከ2 ዓመት በታች ያሉት ቢሆኑም፤ ከዚያ እድሜ በላይ ያሉትም ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ" ነው ያሉት፡፡
ከበጀት አንጻርም ለሕጻናት ተብሎ ለብቻው የሚያዝ በጀት ባለመኖሩ፤ ሕጻናቱን ለምግብ እጥረት እንዲጋለጡ ሊያደርግ ይችላልም ተብሏል፡፡
በእመቤት ሲሳይ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
