
Ahadu Radio And Television
June 16, 2025 at 10:06 AM
*የትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያን ጨምሮ የ36 ተጨማሪ ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሊያግድ ነው*
ሰኔ 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያን ጨምሮ የ36 ተጨማሪ ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ በመከልከል የጉዞ ክልከላውን በከፍተኛ ሁኔታ ለማስፋት እያሰበ መሆኑን ተገልጿል፡፡
በሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተፈርሞ ለዲፕሎማቶች በተዘጋጀው ሰነድ በቀጣይ ዜጎቻቸው ላይ ዕገዳ ሊጣልባቸው የታሰቡ 36 አገራት ዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፤ የሀገራቱ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ሊደረግ እንደሚችልም አመላክቷል፡፡
ከእነዚህ 36 አገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ጅቡቲን ጨምሮ 25ቱ የአፍሪካ ሀገራ ዜጎች መሆናቸውንም ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
በዚህም መሠረት በቀጣይ ዕገዳ ይጣልባቸዋል ከተባሉት የአፍሪካ ሀገራት መካከል፤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ጋምቢያ፣ አንጎላ፣ ታንዛኒያ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ጋና፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ካሜሩን እና ቡርኪና ፋሶ እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም ከመካከለኛው እስያ፣ ከካሪቢያን እና ከፓስፊክ ውቅያኖስ በርካታ ሀገራትም በዝርዝሩ መካተታቸው ተዘግቧል።
"36ቱ ሀገራት የቪዛ እገዳ እንዳይጣልባቸው በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በ60 ቀናት ውስጥ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል" የተባለ ሲሆን፤ ቅድመ ሁኔታዎቹን ካላሟሉ ሙሉ ወይም ከፊል የቪዛ እገዳ እንደሚጠብቃቸውም ተመላክቷል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ዜጎቹን ለማገድ በምክንያትነት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል፤ የዜጎች ማንነትን ለመለየት የሚያስችሉ አስተማማኝ የመታወቂያ ሰነዶችን ለማቅረብ በተጠቀሱት አገሮች ብቃት ማነስ ወይም የትብብር መንግሥት አለመኖሩን የተጠቀሰ ሲሆን፤ ሌላው የፓስፖርታቸው "ደህንነት አጠያያቂ" መሆኑ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም "አንዳንድ ሀገራት ከአሜሪካ እንዲያስወጡ የታዘዙትን ዜጎቻቸውን ለመቀበል አመቺ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ትብብር አልነበራቸውም" የተባለ ሲሆን፤ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ቪዛ አግኝተው ወደ አሜሪካ የገቡ ዜጎቻቸው ለመቆየት ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ መቆየታቸው ለዕገዳው ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሌሎች አሳሳቢ ምክንያቶች ደግሞ "የሀገራቱ ዜጎች በአሜሪካ ውስጥ በተፈጸሙ የሽብርተኝነት ድርጊቶች ወይም ፀረ-ሴማዊ እና ፀረ-አሜሪካዊ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፈዋል" የሚል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
መመሪያው ትራምፕ በዚህ ዓመት በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ላይ የጀመሩት የኢሚግሬሽን እርምጃ አካል ሲሆን፤ ይህም 'የወሮበሎች ቡድን አባል ናቸው' ተብለው የተጠረጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቬንዙዌላውያን ወደ ኤል ሳልቫዶር እንዲሰደዱ መደረጉን እንዲሁም፤ አንዳንድ የውጭ ተማሪዎችን ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ምዝገባ ለመከልከል እና ሌሎችን ለማባረር የተደረገ ጥረትን ያካትታል ተብሏል።
የሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከ12 ሀገራት የሚመጡ ዜጎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክል አዋጅ ፈርመው ማጽደቃቸው የሚታወስ ሲሆን፤ እርምጃው ያስፈለገው አሜሪካን ከ"ውጭ አሸባሪዎች" እና ሌሎች የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶችን ለመከላከል ነው ተብሏል።
በዚህም አፍጋኒስታን፣ ምያንማር፣ ቻድ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ሄይቲ፣ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና የመን ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እናዳይገቡ ዕግድ ተጥሎባቸዋል።
ትራምፕ በመጀመሪያ ጊዜ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት ከሰባት በአብዛኛው ሕዝባቸው ሙስሊም ከሆኑ አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ማገዳቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም የሰሞኑ ዕግድ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
በእዮብ ውብነህ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
