
Ahadu Radio And Television
June 16, 2025 at 10:06 AM
*ከውጪ የሚገባውን የነዳጅ ጥራት የሚያረጋግጥ የምርመራ ማዕከል ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ*
ሰኔ 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባውን ነዳጅ ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችል የጥራት ምርመራ ማዕከል (ላብራቶሪ) በድሬዳዋ ከተማ እንደሚገነባ ትሬድ ማርክ አፍሪካ ለአሐዱ አስታውቋል።
የምርመራ ማዕከሉን ለማቋቋም ከፍተኛ ሙዓለ ንዋይ ፈሰስ የሚደረግበት እንደሆነ የገለጹት በኢትዮጵያ የትሬድ ማርክ አፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት እውነቱ ታየ፤ ለዚህም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መመደቡን ጠቁመዋል፡፡
ሥራውን ለማሳካትም ከኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጋር በመሆን እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጸው፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ነሀሴ ወይም መስከረም አካባቢ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ በነበረው አሰራር ኢትዮጵያ የጥራት ፍተሻውን ለማድረግ የሚያስችላት ላብራቶሪ የሌላት በመሆኑ ናሙናው ወደ ኬንያ እና ሌሎች ሀገራት እንደሚላክ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የነዳጁ ጥራት ተረጋግጦ እስኪመለስ ድረስ አንድ መርከብ አንድ ቀን ሲቆም እስከ 25 ሺሕ ዶላር ስትከፍል መቆየቷን አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩልም "ኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ" ስርዓት የተሰኘ የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድን የሚያሳልጥ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የምርመራ ማዐከሉ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ የኢትዮጵያን የገቢና ወጪ ንግድ መረጃ በማንኛውም ጊዜና ሰዓት ሁሉም ሰው የሚያገኝበትና የሚከታተልበት እንደሚሆን ለአሐዱ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የሎጀስቲክስ ዘርፉን ለማገዝ የሚያስችል ቀደም ሲል የተጀመረ የመርከብ አስተዳደር ሥራ መኖሩን አንስተው፤ ትሬድ ማርክ አፍሪካ አሁንም ሥራው የተሳካ እንዲሆን እያገዘ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
